አፈር ብቻ ነን?

ምትኩ አዲሱ

ለእሑድ ሚያዝያ 13/2005 ዓም ትንሣኤ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኪነ ጥበባት ሰው ሃይማኖት አለሙን ጋብዞ ነበር። ከብጥስጣሽ ምልልሶች በኋላ፣ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ጊታሩን አነሳ።
ጠያቂ፦ (ሃይማኖት) ፋሲካን እንዴት ነው የምታከብረው?
ሃይማኖት፦ “ፋሲካ ሰኞ ነው የተወለድኩት ... የምጫወትላችሁ አርእስቱ፣ ደስት ኢን ዘ ዊንድ ነው። የተወሰደው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ ሁሉ ከአፈር ነው፣ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል ከሚለው መሠረታዊ አሳብ ነው። [1] እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር ካለው ቀን ማለፍ አይቻልም። ብዙ ገንዘብ ቢኖረንም አንድ ደቂቃ እንኳን ያቺን ነገር ማራዘም አንችልም የሚል አሳብ ያለበት ነው ...”

(ሃይማኖት፣ ደስት ኢን ዘ ዊንድን ለምን እንደ መረጠ ማወቅ አይቻልም። የሚገርመው፣ መስከረም 9/2007 ዓም፣ ባመት ከስድስት ወሩ ከዚች ዓለም መለየቱ ነው!)

የአገራችንን ሰው ስለ ሞት ማስታወስ አያሻንም። በንግግሩ በአኗኗሩ በምኞቱ ሳይቀር ሞትን ሳይጠራ ሳያስብ አይውልም አያድርም። በባህሉ፣ ተታኲሶ መሞት ተስማምቶ ከመኖር ይበልጥበታል። ተጋርቶ ከመብላት ሁሉም ጦም ማደሩን ይመርጣል። መቃብርን የዘላለም ቤቴ ይለዋል። በሞት አሳብና ተግባር የመጠመዱ ብዛትና ፍጥነት ሕይወትን አጥብቆ ላለመውደዱ ምስክር ነው። ትንሣኤን ሲያከብር፣ ባብዛኛው የሠራቸው የጽድቅ ሥራዎቹ፣ መፆሞቹ፣ ተበደልኩ የሚልባቸው ሁሉ ተሰባስበው የሰማይን መንግሥት እንደሚያወርሱት ያስባል። ተስፋው እርግጠኛ ተስፋ ይሆን?

ሃይማኖት አለሙ እንዳስተዋለው፣ ልናዘገይ በማንችለው የቅጽበት ሞት ተከብበናል። በሌሎች ላይ የሚሆነው እኛን አይነካን ከመሰለን ራሳችንን ገና እያታለልን ነው።

ከታች የተረጎምኩት ቅኔ፣ ሃይማኖት ያቺን እለት በጊታር ታጅቦ ያዜማት “ደስት ኢን ዘ ዊንድ” የምትለዋ ነች። ገጣሚው፣ አሜሪካዊው ኬሪ ልቭግረን የ ካንዘስ ባንድ መሥራች አባል እና ጊታር ተጫዋች ነው። ኬሪ አንዱን ቀን አንድ የቅኔ መድብል ሲያነብ፣ “ፎር ኦል ዊ አር ኢዝ፣ ደስት ኢን ዘ ዊንድ” የምትል ዘለላ ሐረግ ያገኛል። ሲያስበው እውነትም ሰው ብናኝ አፈር ነው። በዚያን ሰዓት ኬሪ ኑሮ የተሳካለት ሰው ነበረ፤ ብዙ ገንዘብ ሰብስቦ ነበረው። ምን ያደርጋል ታዲያ? ይኸ ሁሉ ወደ አፈር አይደል? አለ። እርሱና ጓደኞቹ ግጥሙን ከሙዚቃ ጋር አቀናብረው በፈረንጆች 1977 አተሙት። ሳይቆይ በገንዘብ እና በዝና ተጥለቀለቁ።

ደስት ኢን ዘ ዊንድ በፈረንጆች ከ2009 ጀምሮ እስከ 2023 (በ14 ዓመታት ውስጥ) በ ካንዘስ ባንድ ዩቱብ ገጽ ላይ ብቻ፣ ሁለት መቶ ስድሳ አንድ ሚሊዮን፣ ስምንት መቶ ሰባ ዘጠኝ ሺህ፣ አራት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ጊዜ ታይቷል/ተደምጧል። ከአንድ ሚሊዮን፣ ስምንት መቶ ሺህ በላይ “ላይክ” ተደርጓል፤ አንዴም እንኳ “ዲስላይክ” አልተደረገም። ለዚህ ምክንያቱ አንድ ብቻ ነው፦ ጥጋብ ካላስረሳው በስተቀር፣ ሰው ሆኖ አፈርነቱን የማያስታውስ የለም። ብዙ ሚሊዮኖች በቅኔውና በዜማው ለመ-ማ-ረካቸው ምክንያቱ ይኸ ነው።

ብናኝ አቧራ ነን

ለሴኮንድ ብቻ ዐይኔን ጨፍኜ
ሴኮንዱ ከምኔው በንኖ ሄዷል
ምኞቴ እያየሁት ከመቅጽበት አልፏል—
ይገርማል

ብናኝ ነው
ሁሉ ብናኝ፣ አቧራ ነው

ድግግሞሽ ማለቂያ የለሽ
ድግግሞሽ ውቅያኖስ ላይ ጠብታ ነው
አንድባንድ ጥረታችን ሁሉ
ልብ አንልም ይንኮታኮታሉ

ብናኝ፣ በነፋስ ፊት ብናኝ ነን
ብናኝ አቧራ ነን

ምንም መቸም አትጠብቅ
ከምድር-ሰማይ በቀር፣ የለምና ‘ሚዘልቅ
ሁሉ አላፊ ነው
ሃብት ቢትረፈረፍ አይሸምትም ደቂቅ

ትቢያ ነው፣ ሁሉ ትቢያ ነፋስ
በነፋስ ፊት ሁሉም ብናኝ አቧራ ነው

ገጣሚ፦ (በእንግሊዝኛ) ኬሪ ሊቭግረን (1977 እ.አ.አ | 1969 ዓም)
ተርጓሚ፦ © ምትኩ አዲሱ (2022 እ.አ.አ | 2015 ዓም)

_____________

አፈር ነን፤ አፈር ብቻ ግን አይደለንም፤ ተስፋ ያለን ሰዎች ነን! ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቷል! የሞትን ኃይል ሽሯል! አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ሕይወትን አብስሯል!

እግዚአብሔር ሰውን ከአፈር አበጃጀው፤ እስትንፋሱን እፍ አለበት፤ አብሮት እንዲኖር ወደደ (ዘፍጥረት 2:7-8)። ሰው ግን ባለመታዘዙ ከእግዚአብሔር ራቀ፤ ‘አታስፈልገኝም፤ ያለአንተም መኖር እችላለሁ’ አለ። ኃጢአት ያ ነው። ውጤቱ፦ ሰው ከራሱ፣ ከጎረቤቱ፣ ከሰላም፣ ከምድር በረከት ተቆራረጠ። በጦርነት፣ በረሃብ፣ በበሽታ፣ በስደት፣ በጥላቻ፣ በፍርኃት፣ ተስፋ በማጣት፣ በሞት ተዋጠ።

ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቀን ኢየሱስ ስለ በደላችን አልፎ ተሰጠ፤ እኛን ስለ ማጽደቅ ከሙታን ተነሳ (ሮሜ 4:25)። በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ የኃጢአት ስርየት እና ምሕረትን አወጀ። አዋጅ የሚሠራው፣ ለሚሰሙ እና ሰምተው ለሚታዘዙ ነው። ሰምተው የታዘዙ ሁሉ ከኃጢአት እሥራት፣ ከሞት ፍርኃት፣ ከኅሊና ወቀሳ ነፃ ይወጣሉ! ወጥተዋል! ባለተስፋ ይሆናሉ፤ ሆነዋል! ይኸ በዘመናት የሚሊዮን ሚሊዮኖች ታሪክ ነው። ኢየሱስ ተነሥቷል! የምሥራች ወንጌል እነሆ!

የኢየሱስ ስቅለት እና ትንሣኤ ለጥቂቶች አይደለም፤ አፈር ለሆነ፣ ሰው ለተባለ ሁሉ ነው፤ ለፍጥረት ሁሉ ነው (ዘፍጥረት 3፤ሮሜ 8፤1ኛ ቆሮንቶስ 15)። በቋንቋ በሃይማኖት በፆታ በሃብት በብሔርና በድንበር ልዩ ልዩ መሆን ለውጥ አያመጣም፤ ኢየሱስ የሞተውና ከሙታን የተነሳው በሞት ፍርኃት በኅሊና ፀፀት ለተጠቃ ሁሉ፣ ለማያምን፣ የልብ የአስተሳሰብ የአነጋገር የአኗኗር ለውጥ ለሚያስፈልገው ሁሉ፣ በጨለማ ላ-ለ ብርሃን ለሚሻ ሁሉ፣ በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረ ሁሉ ምሕረትና ነፃነትን ለማብሠር ነው። መጽሐፍ እንደሚል፣ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ሁሉ እንዲሁ ወድዶአልና (ዮሐንስ 3:16)። “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ ...ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል ...እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤” ምሕረት ሽተው ወደ እርሱ ለሸሹ ሁሉ እግዚአብሔር በደላቸውን አይቆጥርባቸውም። (2ኛ ቆሮንቶስ 5:14፤15፤17፤19)

ኢየሱስን የጥቂት ሃበሾች አሜሪካኖች አውሮጳዎች ግብፆች ፍልስጤም ዐረቦች ሚሲዮኖች መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ብቻ አድርጎ ማሰብ የኖረ ትልቁ ስህተት ነው። የቀደመችዋ የእግዚአብሔር ዓላማ፣በአብርሃም ዘር በኩል የምድር ሕዝቦችን በመላ መባረክ ነው (ዘፍጥረት 22:18)። ኢየሱስን ያመኑ ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ወደ ፊትም ይኖራሉ (ራእይ 5:9-10)። ጉዳዩ፦ ስለ ሰዎች ሃይማኖትና ባህል አይደለም፤ ጉዳዩ፦ ስለ ሕይወት ነው። ይህ ሕይወት ስውር አይደለም ተገልጧል፤ አይሸነሸንም አንድ ነው፤ ኢየሱስ ነው። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም ... መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐንስ ወንጌል 1:3-5፣18)። ጉዳዩ፦ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስለ መውጣት ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የሰጠውን ይቅርታና ሰላም ስለ መቀበል ነው። እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል በፍጹም አሳብ ስለ መውደድ፤ ባልንጀራን እንደ ራስ ስለ መውደድ ነው (ሉቃስ 10:27)።

እግዚአብሔር በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው ሁሉ ፍቅሩን ያሳይ ዘንድ፣ ምህረቱን ይዘረጋ ዘንድ፣ ከኃጢአት ቀንበር ከሞት ባርነት ነፃ ያወጣ ዘንድ ይህ ሆነ። በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደ ዓለም የመጣው የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው ታሪክ እንዲህ ተገልጦ አያውቅም፦ ፍቅሩ እንደ ሰው ፍቅር ውሱን አይደለም፤ ዘመን አያስረጀውም፤ ማንንም አያገልልም፤ ልባቸውን ወደ ከፈቱለት እንደ ጅረት የሚፈሥሥ የማይነጥፍ ፍቅር ነው። ልባቸውን እስኪከፍቱለት ከደጅ ቆሞ የሚያንኳኳ የሚታገስ ቸርና ሰላምተኛ ፍቅር ነው። ኬሪ ልቭግረን፣ ደስት ኢን ዘ ዊንድን ከፃፈ ከጥቂት ዓመት በኋላ የክርስቶስ ተከታይ ሆኗል።

___________

ሰው ሁሉ የሚሰባሰብባቸው መንገዶቹ ይመሳሰላሉ፦ በቤተ ሰብ፤ በመንደር/በአገር፤ በሃይማኖት። ይህም መልካም ነው። ችግሩ ግን እነዚህ ሁሉ ፈጥነው የሚፈረካከሱ ናቸው፤ አያዘልቁም። የሚያዘልቅ ሞትን የሻረ የትንሣኤው ኢየሱስና እርሱ ያያያዘው ብቻ ነው፤ ሞቱ፦ ኃጢአት የሚያስከትለውን ፍርድ ያሳየናል። እስከ መስቀል ሞት ድረስ ሰውን የመውደዱን ጥልቀት፣ የምሕረቱን ስፋት ያወርሰናል። ትንሣኤው፦ የተስፋውን ዘላለማዊነት። የእግዚአብሔር ፍቅር በልቡ ያለው፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሁሉ እንደ ራሱ መውደድ ይጀምራል። ይኸኔ ብቻ፣ ሰው ለራሱ ለባልንጀራውና ላገሩ ይበጃል። ጆሮ ያለው ይስማ!

[1]አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” (ዘፍጥረት 3:19)። መጽሐፈ መክብብ (1:14፤ 2:11)፦ “ሁሉ ከንቱ ነው፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” (3:20)፦ “ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።” (12:7)፦ “አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።” ይላል።

© ሚያዝያ 2016 ዓም | April 2024 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.

እሳት ነው፣ በእሳት ነው | ኅብር ሕይወቴ | የማርያም ታላቅ አእምሮከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ