ዝናብና መጽሐፍ

በምትኩ አዲሱ

rainድንገት ዶፉን ሲለቀው ጊዜ፣ ሁላችንም እየተሰባበርን እፊታችን ወዳለው መጠለያ ለመድረስ ተሽቀዳድመን ሮጥን፤

ገሚሱ ሰው በስተ ግራ በኩል ካለው የልብስ መደብር ተንጋግቶ ገባ፤ እኔም ከቀሩቱ ጋር በስተ ቀኝ ካለው የመጽሐፍት መሸጫ ዘው አልኩ፣

የዝናቡ ምሬት ሺህ ቦኖ ውሃ የተከፈተ ይመስል ይወርድ ጀመር። በንዲህ ያለ ሰዓት ቤተ መጽሐፍ ውስጥ መገኘት ምንኛ መታደል ነው? እንግዲህ ቢሻው እንደ ኖኅ ዘመን አርባ ቀንና አርባ ለሊት ይልቀቀው … እኔ እንደሆንኩ፣ የማልዘልቀው ሁዳድ ሙሉ መጽሐፍ አግኝቻለሁ!

አብረን ከተሰደድነው መካከል አንድና ሁለቱ ብቻ መግቢያው አጠገብ ያለውን መደርደርያ አየት አድርገው መለስ ብለዋል፤ ምን የሚያስጠይፍ ነገር እንዳገኙበት እንጃ፤ የተቀሩቱ በርና በረንዳው ላይ ጀርባቸውን ሰጥተው ደጅ ደጁን ትክ ብለው እያዩ በአሳብ ተውጠዋል። ሲጃራ ከሚያጤሱትና አልፎ አልፎ ከሚያስላቸው በተቀረ ንግግር የለም። … ባመትባል ገበያ ካፊያ መታረዱ ታስቦት ራስ ለራስ ገጥሞ እንደ ቆመ የበግ መንጋ እጅብ ብለው ቆመዋል። መጽሐፍቱም በየዓይነታቸው ተሰልፈው አላፊ አግዳሚውን በትዝብት ይቃኛሉ፣ ወዳጅነታቸውን ለሚሻ ራሳቸውን ያቀርባሉ፣ ችላ የሚላቸውን ደግሞ ልብ እስከሚገዛ በትግስት ይጠብቁታል።

የመጽሐፍት ቤት በመሠረቱ የሥነ ስርኣት ክልል ነው፤ እና ስለ ሥነ-ታሪክ የሚያወሳውን ልብ ወለድ ተራ መፈለግ ትርፉ ድካም ነው። በአንጻሩ ሃይማኖትና ፍልስፍና-ነክ ጽሑፎች ከክሕደትና ኑፋቄ ጋር ተደርድረዋል፤ … ክሕደትና ኑፋቄም እኰ ለተያያዙት ሃይማኖት መሆኑ ነው።

ለሕፃናት የተጻፉት ከአዋቂዎች መደዳ አይደረደሩም፤ መጽሐፎቹን የጻፉት አዋቂዎች ሆነው ሳለ ለምን እንደዚህ እንደሆነ ከቶ ሊገባኝ አልቻለም፣ ደግሞስ አዋቂ ከልጅ አይማርም ያለ ማነው?

በአንጻሩ ጥንታዊ ትምህርትና ዘመናዊው ጐን ለጐን ትከሻ ገጥመው ተሰልፈዋል። ይህም ተገቢ ነው፣ እንደ እውነቱ ከሆነ የጥንት ሰዎች ከጠየቁት የተለየ ምንም አዲስ ጥያቄ ተጠይቆ አያውቅምና። ያው የሰነበተው፣

እኔ ማን ነኝ?

ከየት ተገኘሁ?

የምኖረው ለምንድነው?

መጨረሻዬስ ምን ይሆን? አደል?

ልማድ ሆኖብኝ መጽሐፍት ቤት በገባሁ ቁጥር መጀመሪያ ለብ-ለብ አሰሣ አደርጋለሁ፤ እንደ ሁኔታውና እንደ ሰሞኑ ስሜቴ የምፈልገው ርዕስ ጋ እስክደርስ የመጽሐፉን ዐቢይ ክፍሎች እየቃኘሁ ግራና ቀኝ ታጅቤ ሽር ሽር እላለሁ፤ ለብ-ለብ አሰሣ ይኸ ነው። ከዚያ ለብ-ለብ ንባብ እጀምራለሁ፤ እግረ መንገዱን ሰው የቆየ ወዳጁን መንገድ ላይ አግኝቶ ለሰላምታ ቆም እንደሚል ቆም እያልኩ አንድ ሁለቱን ገጽ እሳለማለሁ …

“ታሪክና ምሣሌ” በከበደ ሚካኤል። እስቲ ምን ይል ይሆን?

አንድ ቀን ተጣልተው ክረምትና በጋ

እንድፈርድላቸው መጡ ወደኔ ጋ …

ከለታት አንድ ቀን በአንዲት ከተማ

የገጠር አህያ መሃል መንገድ ቆማ

መኪና መጣና ድምፁን ሳትሰማ

ጨፍልቆ አሳረፋት ውሃ ሳትል ደክማ፣ (ባለአህያው የመኪናውን ጎማ በጅራፍ ሲዠልጥ ይታያል)

ከዚኛው መደርደሪያ ጫፍ ላይ ቀጥ ብሎ የቆመው ደግሞ፣ “መጫፈ ቁልቁሉ” ይላል። የት እንዳነበብኩ ባላስታውስም የትርጉምና ሥነ መለኰት ሊቅ ስለ ሆኑት ስለ ኦነሲሞስ ነሲብ የሆነ ታሪክ አንብቤአለሁ፤ በዚያ ጽሑፍ ላይ እንደ ሰፈረው ከሆነ የልጅነት ስማቸው “ሂካ” ነው። እንግዲህ ሙሉ ሰው ሆኖ እንደ ስሙ የኖረ አንድ እርሳቸውን ሰምቻለሁ፤ ኧረ አንዳንዱንስ እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ምልክት ያደርግበታል ወይ?

ቀጥሎ፣ “ድግሪ ያሳበደው” ይላል። … (ከዚህስ እግዜር ይጠብቀን)

“ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በቀ.ኃ.ሥ፣ “አርሙኝ”

“ሌላው መንገድ”፣ ወዲያው ቀጥሎ፣ “አደፍርስ”

“ለማና ዘመዶቹ”፣ “ለማ በገበያ”፣ “ለማ በትምህርት ቤት” (የዛሬ ትምህርት እንዲህ ሸቀጥ ሊሆን)

“ወዳጄ ልቤ”፣ “ጆሮ ጠቢ”፣ “ሰው አለ ብዬ”

“አማኑኤል ደርሶ መልስ”፣ … (መመለሱ በጀ)

“አረንጓዴው ጓደኛዬ” (ይኸ የእንግሊዞች እጅ አለበት)፣ “የዕውቀት ብልጭታ”

“ልጅነት ተመልሶ አይመጣም”

“እንደ ወጣች ቀረች”

“ማነው ኢትዮጵያዊ?” በታደለ ገብረ ሕይወት፣

“ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” (ምን አደከመህ? ይህንማ ጉራጌ ዘመዶቼ ይነግሩህ የለ?)

“የኅሊና ደወል --- 1966” በበዓሉ ግርማ፣ የ-ኅ-ሊ-ና ደ-ወ-ል …?

ቀጥሎ፣ “እሳት ወይ አበባ --- 1966” … (ይኸ ደግሞ ጭንቅ ሰዓት፣ ጭንቅ ምርጫ ነበር፤ … እኛም እሳት መረጥን። ከሃያ አመት በኋላ፣ ትውልድ ተላልቆ፣ የቀናው ካገር ተሰዶ ይኸው ዐመድ ወለድና) ። … ለማንኛውም እስቲ ዜማ ጸጋዬን ልከልስ፤

ቢራ ቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ

ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ፣ አቅፈሽ መመሰሉ

ለምንድነው ቢራ ቢሮ

አበባሽ ከአበባው ሠምሮ፣

በፀደይ ከዐደይ ጋር ፈክቶ

በርቶ፣ ተጥለቅልቆ ደርቶ

እንደ ጮራ ተንዠርግጎ፣ በመንጸባርቅ ተንጣሎ

ፀደይ አክሎ ፀደይ መስሎ

ውሎ፣ ኋላ ቀኑ ሲመሽ

ፀሐይ ግንባሯን ቀልሳ፣ ከጭለማ ክንፍ ስትሸሽ

ብርሃኗ በሌት ተዳፍኖ፣ ዓይኗም ፈገግታዋም ሲሰንፍ

አዝርእቱ እርጭ ብሎ፣ ጸጋውን ከመልኩ ሲገፍ

አበባው ምድሩን ሲንተራስ፣ ያፈር ጽዋ ዕረፍቱን ሲገድፍ

ቢራ ቢሮ ያንቺስ ሞገስ፣ ለምንድነው አብሮ

እሚረግፍ? …

ምን አይተሻል ከቄጠማ፣ ምን አይተሻል ከለምለሙ

ቀን አብረሽ አብበሽ ውለሽ፣ ሲመሽ አብረሽ

መስለምለሙ? …

አስተምሪኝ ቢራ ቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ? …

ዝናቡም እንደ አጀማመሩ ሳያስታውቅ ቀጥ አለ ---- ፈጣሪ ለፍጥረቱ ምን እያለ ይሆን …. ? ወዲያው የሰው ኰቴ እንደ ጭራሮ ይተረማመስ ጀመር፤ ጥቂቶች የሸመቱትን ልብስ በጉያቸው ይዘው ሁሉም እንደገና አውራ መንገዱ ላይ ፈሰሰ ….

©1997 by Mitiku Adisu