ችግር ችግር ይወልዳል፤ ችግር መፍትሔ ይወልዳል፤ መፍትሔ ችግር ይወልዳል

በምትኩ አዲሱ

የአሳብ ልዩነት ከክርስቶስ ማህበር ፈጽሞ የተወገደበት ዘመን የለም። ዓለም፣ ሥጋና ሰይጣን ተሽረው የትንሣኤ አካል እስክንለብስ፣ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እስክትወርድ”ና እስክንገባባት ድረስ ይህ ሁኔታ የሚቀጥል ነው። “የገሃነም ደጆች አይችሏትም” ሲል የሚፈታተኑ የጨለማ ኃይላት አሉ፣ ሆኖም የክርስቶስን ማህበር ሊያሸንፉ አይችሉም ማለቱ ነው። “ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም” [ዮሐንስ1፡5]። የሚታየው ሁኔታ ትእግስት አስጨራሽና ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል ይችላል። የጸጋ ሁሉ ባለቤትና የቤተክርስቲያኑ ራስ ኢየሱስ ሕያው ስለሆነ ብቻ ተስፋ አንቆርጥም።

ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ይዘት በየማህበራቱ ለተከሰቱ የሞራል ውድቀቶች፣ የስህተት ትምህርቶች ወይም አስተዳደራዊ ቀውሶች እርምትና ማጽኛ የሚሆኑ መመሪያዎችን መስጠትና ማስተማሩን ማሳሰብ ነው። ይህን ጠንቅቆ ማወቅ፣ “ክርስቲያኖች ደግሞ እንዲህ ናቸው እንዴ?” ከሚል ግራ ከተጋባ ጥያቄ ሊጠብቅ ይችላል።

ችግሮች ገንቢ የሆነ ገጽታ አላቸው። ለሚያስተውሉ እድገት ይጨምራሉ። የሰዎችን የተደበቀ ባህርይ ስለሚገልጡ፣ ለጌታ ሥራ የሚበጁትንና የማይበጁትን ማህበሩ እንዲለያቸው አስተዋጽዖ ያደርጋሉ። የተያዘውን አሠራር ለማሻሻል፣ ዓላማን አጥርቶ ለማየትና ለማጽናት ይጠቅማሉ። ሆኖም ቅንነት ከሌለ መፍትሔም እንኳ ሌላ ችግር መውለዱ አይቀርም። ለዚህ በዋነኛነት ተጠያቂ የሚሆኑት መሪዎች ናቸው። እንግዲህ፣ ጥያቄው ማተኮር ያለበት፦ “ችግር ከመፈጠሩ ወይም ከመባባሱ በፊት እንዴት ማስቆም ይቻላል? አፈታቱ እንዴት ይሁን? እንዳይደገም ምን ጥንቃቄ ይወሰድ?” በሚለው ላይ ነው። ችግር የሚባባሰው ከአያያዝ ነው፤ ካለፉት ሁኔታዎችና ከሌሎች ልምድ ሳንማር ስንቀርና ከአዳም የወረስነው ጠባሳ በዚህኛው ዓለም እንደማይሽር ስንዘነጋ ነው።  

የክርስቶስ ማህበር ከተለያየ የሕይወት ልምድ፣ ባህልና አስተዳደግ የተውጣጡ እና በተለያየ መንፈሳዊ እድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ስብስብ ነው። ኢየሱስ ያመኑትን በበግ ይመስላቸዋል። የእረኛውን ድምጽ የሚለይና ከእረኛው መራቅ የማይሆንለት አለ። ታውኮ መንጋውን የሚያውክ አለ። ከተከለለለት አልፎ መባዘን የሚያበዛ አለ። እንዳይጨነግፉ ወይም ብርቱዎች እንዳይረጋግጡአቸው እንክብካቤ የሚያሻቸው አሉ። ያመኑትን በመሬትም ይመስላቸዋል። ከነዚህም የተመቸ ልብ ያላቸው ዘሩን ተቀብለው ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ፣ በተገኙበት ሁሉ የሰላም ሲሳይ የሚያመጡ አሉ። የስሜት ግለት እንጂ ጠልቆ ያልገባቸው አሉ። የዓለሙንና የሰማዩን ሕይወት አጣምሮ መያዝ የሚሻ ልብ ያላቸው አሉ። እውነቱን ቢያውቁም ለእውነት መቆም የሚሳናቸው አሉ፤ እነኝህም በእግዚአብሔር ሳይሆን በሰው ፍርኃት ወጥመድ የተያዙ ናቸው። ታዲያ፣ ሁሉም በጸጋው የዳኑ ናቸው። ሁሉም ለጌታ ልጆቹ ናቸው። የሁሉም መታዘዝና መረዳት ግን እኩል ነው ማለት አይደለም። አስቸጋሪ ልጆች አሉ፣ ጨዋዎች አሉ። ስለ ክርስቶስና ስለ ቤቱ ያለን መረዳትና አክብሮት እንደዚሁ አንድ ወጥ አይደለም። ራስ ወዳዶች ነን። የሌላውን ጉድፍ ማየትና ማጉላት ይቀናናል። ራሳችንንና የኛ የሆኑትን ማስቀደም ይቀለናል። ራሳችንን ማየት በብዙ ይሳነናል። ገሮች እንዳሉ ሁሉ ክፉዎችም በክርስቶስ ማህበር ውስጥ አሉ፤ “የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ፣ የሚያታልሉም …በቃልም የሚጣሉ፣ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነው …ቃላቸው እንደ ጭንቁር ይባላል” ይላቸዋል፤ [2ጢሞ4፡14-15።ቲቶ1፡10-11።2ጢሞ2፡14-17]

ከአንድ አማኝ ደግሞ የሚጠበቁ መሠረታዊ ሥነ ምግባሮች አሉ። በክርስቶስ ያመኑትን፣ ወንጌል “የብርሃን ልጆች” ይላቸዋል። እነዚህ የብርሃን ልጆች ከጨለማ ሥልጣን ሥር ክርስቶስ ነጻ ያወጣቸው ስለሆኑ ተመልሰው በጨለማ ሥራ ሊሰማሩ አይገባም። የቤቱን ሥርዓት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው። ሊታዘዙ እንጂ እንዳፈቀዳቸው ሊሆኑ አይገባም። ከሥጋ ሥራ ከ“ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ ወዘተ” መቆጠብ ይኖርባቸዋል [ገላትያ 5፡19-20]። ጸጋና ሰማያዊ ጥበብ መለመን ይጠበቅባቸዋል።

“ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፣ ነገር ግን የምድር ነው፣ የሥጋም ነው፣ የአጋንንትም ነው። ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና… ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል … ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት” [ያዕ.1፡5፤3፡14-17]

ሳዖል [ኋላም ጳውሎስ] ለእግዚአብሔር የቀና መስሎት የቅዱሳንን ማህበር ያውክና ያጎሳቁል ነበር። የ”ብርሃን” ሥራ የሠራ መስሎት። ለጨለማ ኃይላት መሣሪያ እንደ ሆነ አላወቀም። ክፋት ከክፉው ነው። ክስ ከወንድሞች ከሳሽ ነው። ሐሰት ከሐሰት አባት ነው። አመጽ ከጽድቅ ጠላት ነው። እውነትን ከሐሰት፣ አመጽን ከጽድቅ መለየት ሲያቅት ይህ የሚያስፈራ ጨለማ ነው። ሳዖል እግዚአብሔርን በትጋት ያገለገለ ይመስለው ነበር። በጽድቅ መንገድ ላይ ራሱን ያለማመደ ይመስለው ነበር። የላቀ ቅናት ያሳየ ይመስለው ነበር። ይመስለው ነበር። “የአምልኮ መልክ አላቸው፣ ኃይሉን ግን ክደዋል፤” [2ኛ ጢሞ3፡5] የሚያይ ይመስለው ነበር፣ ዓይኑን ቅርፊት እንደ ሸፈነው አላወቀም! ክርስቶስን አይቶ ግርዶሹ ከዓይኑ ላይ እስከረገፈለት ድረስ በጥፋት ጎዳና ላይ እንደ ሆነ አላስተዋለም። ሰው ቢነግረው የሚሰማ አልነበረም። ኢየሱስ መንገዱ ላይ ቆሞ ከተቀመጠበት ከፍታ ላይ ወደ ታች እስኪጥለው ድረስ። ለሳዖል ከጥፋት መንገድ መመለስ ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፦ የመጀመሪያው፣ “ኧረ አንድ በል እንጂ ስለዚህ ሰው፤ አወከ፣ አሸነፈ እኮ!” እያሉ አጥብቀው የሚጸልዩ ቅዱሳን ነበሩ። ሁለተኛው፣ ሳዖል ራሱ እውነቱ ይብራለት እንጂ ከአመጻ ለመመለስ የሚፈቅድ ልብ ነበረው። ኢየሱስም ይህን አይቶ ራራለት፣ እመንገዱ ላይ ደርሶ አገኘው። መንፈሳዊ ዕውርነት ለመመከር ካለመፍቀድ፣ ራስን ከማታለል አልፎ ሌሎችን ከማታለል፣ ደጋግሞ የቃሉንና የመንፈስ ቅዱስን ብርሃን ካለመታዘዝና ከመግፋት የሚመጣ ነው። ጳውሎስ ኋላ ከመንፈሳዊ እብደቱ ሲመለስ በተራው በኤፌሶን ለሚገኙ ቅዱሳን “የልባቸው ዓይኖች እንዲበሩ” ጸልዮላቸዋል [ኤፌ1።19]። ሰው ለራሱ ቢፈራ ያስተውላል።

በፍጻሜ ላይ “ከቶ አላወቅኋችሁም” የሚባሉ አሉ [ማቴ 7፡21-23]። ከእነዚህም አንዳንዶች ትንቢት የተናገሩ፣ ተአምራት ያደረጉ፣ የሰዎችን ሙገሣ የተቀበሉ ናቸው። “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ” ማለታቸው ከአፍ ያለፈ ስላልሆነ፦ “እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ይባላሉ። በክርስቶስ ማህበር ውስጥ እንግዲህ ብዙ ዓይነት ሰዎች አሉ።

“ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ” [መዝ19፡12-13]። ክርክርን ለመፍታት በመጀመሪያ፣ መንስዔውን ለይቶ ማወቅ፣ ከማህበሩ ሕይወት መታነጽ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ማጣራት ያስፈልጋል። ሁለተኛ፣ የግል ጉዳይ እንዳይመስል ከሰዎች ጋር አለማያያዝ፣ ሁኔታዎችን ነጣጥሎ ማየት ያሻል። ማንም ሰው ይሳሳታል፣ ያለማ መስሎት ያጠፋል። ሁሉም ይሳሳታል ስንል ግን ስህተትን ላለመቀበልና ማንም ከማንም ስለማይሻል ማንም ምንም ለማለት መብት የለውም ለማሰኘት መሆን የለበትም። ሁሉም ሊያከብረው እንጂ ሊተላለፈው የማይገባው የቃሉ ሥልጣን ድንበር አለ። አንድ ማህበር የጥቂቶች ጉዳይ ስላልሆነ፣ በጥቂቶች ፈቃድ መታሰር የለበትም። እና፣ ለክርስቶስ ማህበር የሚበጀው፣ የሚያስፈልገው አንድ ወይም ጥቂት ነገር ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ያሻል። ሦስተኛ፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የቱ ነው? ብሎ መጠየቅ። በጥቃቅኑ ጊዜና ጉልበት ከመፍጀት ይልቅ፣ የማህበሩ ቀዳሚ ዓላማ ያም፣ በክርስቶስ እውቀት ማደግ፣ አብሮ ማደግ፣ ሌሎችን በወንጌል መድረስ መሆኑን አጉልቶ ማሳየት። በክርስቶስ እውቀት ማደግ ማለት ሁሉም የመሰለውን [የሰማውንና የተሰማውን] አብዝቶ መናገር ሳይሆን ቃሉን በተያያዘ መልኩ በግልና በማህበር ትሑትና ለመታዘዝ በቆረጠ ልብና አእምሮ መቀበል ማለት ነው።  “በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ፤” ተብለናል። [1 ቆሮ 1420 ኤፌሶን 18 423 በተጨማሪ ያንብቡ] አራተኛ፣ ሊተላለፉ የሚገባቸውን አሳቦች ወቅታዊ፣ ቀላልና ግልጽ ማድረግ። አምስተኛ፣ ሁሉን፣ ሁሉን ለሚችል አምላክ መተው። እግዚአብሔር አይዘበትበትም። እነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ የመፍትሔውን አቅጣጫ ይወስናሉ፣ 1/ በማህበሩ መካከል ፈቃደኛነት አለ? [ፈቃደኛነት ከሌለ እግዚአብሔር በአካል ቢገለጽም እንኳ የማይመለሱ አሉ] 2/ ተናጋሪው ወይም አሳብ አቅራቢው ማነው? 3/ መነሻ አሳቡ ምንድነው? 4/ ስለዚህ ጉዳይ ቃሉ ምን ይላል? ኅሊናስ? በውስጣችን ያሳደረው የክርስቶስስ ሰላም? 5/ እኔስ አቋሜ ምን ሊሆን ይገባል?

እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ስለሆነ ሁሉ በሥርዓት ሊሆን ይገባል [ማቴዎስ 18]። አንጃ መፍጠር፣ ስም ማጥፋት ማህበሩን በወሬና በአሉባልታ ማወክ በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ስም በተሰየመው ማህበር ፊት ጸያፍ ነገር ነው። የአሳብ ልዩነትም እንኳ ቢኖር በግል የተነጋገረውን ያለ ሰዓቱና ያለ ቦታው ማውራት ወይም መካድ አለመታመን ነው። ማህበርተኛም በበኩሉ አሉባልታን ማስተናገድና የሰማውን ማስተጋባት የለበትም። በዚህ ተግባር የተሰማሩትን ፊት መንሳት፣ ማህበሩን በሚያንጽ ጉዳይ ላይ መረባረብ ይገባል። “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ” ብሏልና [ኤፌሶን 5፡11]። ከቃሉ አኳያ አቋም መውሰድ ደግሞ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም።

“በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ሰውን ከአባቱ፣ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፣ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና …ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። መስቀሉን የማይይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” ያለው ለጽድቅ መቆም ወዳጅ ሊያሳጣ እንደሚችል ለማስረዳት ነው፤ ከሰዎች ወዳጅነት የእግዚአብሔር ወዳጅነት ይበልጣልና። እግዚአብሔር ወዳጅ ሲሆን የሰው ወዳጅ አይነሳም [ያውም ከወንድም የሚጠጋጋውን]። የሰውን ወዳጅነት ማስቀደም ግን የእግዚአብሔርን ወዳጅነት ማቃለል ነው። [ማቴ 10፡ 34-39]

በሐዲስ ኪዳን ማህበራት ውስጥ ክርክርና ድንጋጤ ያስነሱ ሁኔታዎችን መመልከት ይጠቅማል። “እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ” ባሉበት ወቅት [ማር10፡31-]። “እኔ የጳውሎስ፣ እኔ የኬፋ፣ እኔ የክርስቶስ” ሲሉ። “የላቀ መንፈሳዊነት” የተሰማቸው ሰዓት። [1ኛቆሮ1፡11-13] እግዚአብሔር ያላየ መስሎአቸው ሲዳፈሩና ሲያታልሉ [የሐዋሥራ 5]። “ዋነኛ” መሆን ሲቃጣቸው [የሥልጣን ሽሚያ ሲኖር፤ በጸጋ ሳይሆን በሰው ብልሃት እግዚአብሔርን ለማገልገል ሲሞከር]፦

“ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ፥ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፥ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል። ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም” [3ኛይቱ የዮሐንስ መልእክት 9-11]

ባጭሩ፣ ችግሮች የሚመነጩት፣ ለክርስቶስ መንፈስ ካልተገዛ ሥጋዊ ሕይወት ውስጥ ነው [ያዕ. 4፡ 1-4]። የነዚህም መንፈሳዊነት ቃሉን ከማነብነብ አልፎ የሥነ ምግባር ለውጥ የማይታይባቸው ናቸው። በክርስቶስ ያመኑቱ፦ ገርነት፣ የእግዚአብሔር ፍርሃትና፣ ለሰው አክብሮት ሊኖራቸው ይገባል። ቅድም እንዳነሳነው የክስ ምንጩ የወንድሞች ከሳሽ ነው። ክፋት ከክፉው ነው፤ ስውር ሥራ ከጨለማ ኃይላት ነው። እነዚህን በመሳሰሉ ተግባሮች የሚሠማሩ ከአጋንንት ጋር እየተባበሩ እንደ ሆነ አያስተውሉም፤ ለመንፈስ ቅዱስ ሁለንተናቸውን ካላስገዙና በጸሎት ካልተያዙ በተቀር ለጥፋትና ለሁከት መተላለፊያ ይሆናሉ። እንደ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደ ይሁዳ። ከበዓለ ሃምሳ በፊት እንደ ነበረው እንደ ጴጥሮስ። የሚዋዥቅ አቋም አላቸው፤ አንድ እግራቸው በዓለም፣ ሌላኛው በክርስቶስ ደጅ ነው። ገና ያልረገፈላቸው የዓለም ዐመል ተጭኖአቸዋል። መጽሐፍ ግን በከፊል ሳይሆን ጠቅልለህ ተሰጥ ይለናል፦ “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሐር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” አሠራርን አለማወቅ፣ ለማወቅና ለመታረም አለመፍቀድ ሌላው የችግር መንስኤ ነው።

የማህበርን አንድነት የሚፈታተኑትን ከታች በተመለከተው መሠረት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ይህም ዛሬ የታየ ሳይሆን ጥንትም የነበረ ነው። 1/ የቤተክርስቲያንን ሥልጣንና ማንነት አለማወቅ 2/ የሞራል ውድቀት ሲኖር [1ቆሮ 5-7፤ 5፡9-13] 3/ የእግዚአብሔር ቃል መካከለኛነቱ ሲዛነፍ [1ኛ ቆሮ 8፡1-13]፤ መንፈሳዊነት “ነኝ” ብቻ ሲሆን፣ እግዚአብሔር ሳይናገር “ተናገረኝ” ማለት ሲበዛ፣ “መንፈሳዊነት” ለመኩራሪያና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሲውል፤ እግዚአብሔር “ይህን አለ” ሲሉ፣ እግዚአብሔር እንደማይሰማ፣ ቀጠሮ እንደያዘላቸውና ማለቱንና አለማለቱን የሚለይ መንፈስ የተሰጣቸው እንዳሉ መዘንጋት 4/ ምዕመኑ የእግዚአብሔርን አሳብ ከስሜቱ መለየት ሲሳነው 5/ በመሪዎች መካከል አለመተማመን ሲጠፋ፣ ወደ ምዕመን ሲዛመት [1ቆሮ1፡10-11፤ 3፡1-2]

መሪዎች ሕዝቡን አቅጣጫ ለማሳየት፣ ኃላፊነት ለማከፋፈል፣ ጸጋን ለማነሳሳትና መተማመንን ለመፍጠር ይሾማሉ። ካልሆነ ግን በሚፈጠረው ክፍተት ቅንነት የጎደላቸውና ያልተገባቸው ሰዎች ገብተው ሥራውን  ማጎሳቆላቸው አይቀርም። አንድ ማህበር የአቋሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊነት የሚገመገመው ምዕመኑ፦ ክርስቶስን በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ ሲደርስ ነው። ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን እንዲሆን …በቃሉ ላይ የተመሠረተና የተደላደለ፣ ከተቀበለው የወንጌል ተስፋ በሆነ ባልሆነ ነፋስ ሳይናወጥ ጸንቶ ሲገኝ ነው። [ኤፌ4፡12-14፤ቆላስ1፡23] ከዚህ የሚያስተጓጉሉ አስተሳሰቦች ደግሞ አሉ፦ 1/ ችግሮች በራሳቸው ተንነው ይወገዳሉ ብሎ ማሰብ 2/ “ሌሎቹ እንዲፈሩ ማህበሩን የሚያውኩትን በሁሉ ፊት” አለመገሠጽ [1ጢሞ5፡20] 3/ በግል ኑሮ ከመሸነፍ የተነሳ ሙሉ ለሙሉ አለመሰጠት 4/ ለጽድቅ ነገር አለመጨከን። ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰዎችን መፍራት፣ ተመሳስሎ መኖር። ጳውሎስ የጴጥሮስን የበርናባስንና የሌሎችን ግብዝነት “በሁሉ ፊት ባይቃወም” ኖሮ የወንጌል እውነት ይበረዝ ነበር [ገላ 2፡11-14] 5/ የአማንያንን ጸጋ አለማነሣሣት 6/ ግልጽነትና ተጠሪነትን አለማጽናት። መልካካም የሆኑ የጸጋ አሳቦችን በአስተዳደሩ የጎደለውን ለመሸፈኛ በ“ራእይ” ማሳበብ፤ ጉባዔን በ “ቃል ኪዳን” ማሠር፤ ሽማግሌ [“ኮሚቴ”]፣ የተቀባ/ሐዋርያ እያሉ መነጣጠልና ከተጠሪነት መሸሸጊያ መፍጠር 7/ “አምልኮ” ላይ ያተኮረ፣ ለቃሉና ለደቀመዝሙርነት ያነሰ ጊዜ የሰጠ አሠራር ማስቀደም፤

ችግሮች በአብዛኛው ከሰዎች ብርቱ ፈቃድና ምኞት ውስጥ ይመነጫሉ። “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ፣ ለእናንተም አይሆንም፣ ትገድላላችሁ፣ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ” [ያዕቆብ 4፡1-4]። መፍትሔም በዚሁ ክፍል ላይ ተመልክቶአል። ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገውን እግዚአብሔር “ይቃወማል” ይላል። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። ትሑታን የክርስቶስ ልብ ያላቸው ናቸው፤ ራሳቸውን ለክርስቶስ ያስገዙ ናቸው። ለክርስቶስ ስለ ተገዙ ለጉባኤ ይገዛሉ። ሁሉን ለሚገዛ ራሳቸውን ስላስገዙ የሁሉ ጌታ የሆነው ሁሉን ያስገዛላቸው ናቸው። [ሉቃስ 22፡24-27፤ ዮሐንስ 13፡12-17 ይመልከቱ]  

ሰዎች ስንባል ለውጥ ያስፈራናል፤ የያዝነውን ላለመልቀቅ እንታገላለን፤ በሌሎች ላይ መሠልጠን ይቀናናል። ካስፈለገ ራሳችንን ማግለል ማስተዋልና ትሕትና ሳይሆን መሸነፍ ይመስለናል። ያለ እኛ የሚሆን አይመስለንም። ያልተረዳነውን ሁሉ በደፈናው እንነቅፋለን። አንድ የቅዱሳን ማህበር የሚገጥሙትን ችግሮች የመፍታት አቅሙ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት ላይ የመታነጹን ያህል ነው። የጽድቅ ሥራ እንዲሠራ አመጽን የሚቋቋም ጉልበት ሲጠፋ፣ ማህበሩ ይታወካል እንጂ እረፍትን አያገኝም። ተመልካች ብቻ የሆነ ጉባዔ ወተት ከመጋት ያላለፈ ጉባዔ ነው፤ ማንኛውም የትምህርት ነፋስ የሚወዘውዘው ይሆናል። ምዕመን ተመልካች ሲሆን፣ የተባለውን ከመቀበል አልፎ ጥያቄ መጠየቅ ሲሳነው፣ በአመራር ላይ ያሉት ኃላፊነታቸውን እንደ ዘነጉ አስረጅ ነው። የክርስቶስ ማህበር ሥራ እንዲቀና ፈቃደኛነት ሲጠፋ፣ የተካረሩ ወገኖች ለጌታ ሥራና ለመንፈስ ቅዱስ አልመች ሲሉ፣ እያንዳንዱ ከራሱ አልፎ የማህበሩን ኅልውና በስፋት ማየት ሲያቅተው፣ በመሪነት ሥፍራ ላይ የተቀመጡም የሚያደርጉትን ሳያውቁ ሲቀርና ወሳኝ መሆን ሲያቅታቸው፣ እያንዳንዱ እውነቱ ከኔ ጋር ነው ማለት ሲያበዛ፣ ያኔ የሚያስፈልገው ሰው ሳይገባበት ድንገት ደርሶ በምልክት እንዲገላግል የቤቱን ጌታ በጸሎት መጣራት ነው።                    2010/2012