የመጨረሻው ዘመን ስህተት አሠራሮችና ጥንቃቄ [ክፍል 1]
በሰለሞን ከበደ
“መጻሕፍትንና የእግዚአብሔር ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ” (ማቴዎስ 22፡29)
ያለንበት ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተለያዩ የፀጋ ስጦታዎች የሚታዩበት ነው፤ በአንጻሩ በተመሳሳይ መንገድ የቀደመው እባብ ራሱን እንደ ብርሃን መልአክ በመለወጥ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳት የተነሳበት ጊዜ ነው፤ ቃሉ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” እንደሚል በማስተዋል በጥንቃቄ ልንመላለስ ይገባል (ማቴዎስ 24፡4)። ሃሰት በዙሪያዋ፣ በአጠገቧና በመካከልዋ እየበቀለ ቢያውካትም፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን “የእውነት ዓምድና መሠረት” ናት (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡14)። ብዙዎቻችን የመንፈሳዊ እንቅስቃሴን ትምህርትና ትክክለኛነት ከራሳችን ስሜት፣ ልምድ፣ የግል ጥቅም፣ ምቾት፣ ክብር፣ የባህርይ ዝንባሌ ውጪ የምንለካበት ሚዛን ይኖረን ይሆን? አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ የመፈተሽ ባሕል አዳብረን ይሆን?
ልብ መባል የሚገባው በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴን መመዘን እንቅስቃሴን ለማንኳሰስ ሳይሆን የጠራውን ለመያዝና በዚህም ለመገልገል ከሚፈልግ እውነተኛና ቅን ልብ የተነሳ መሆን አለበት። አንዳንዶች ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ (በፀጋ ስጦታዎች መገለጥ) ስለማያምኑ ለማጣጣል መቃወሚያ ምክንያቶችን ይፈልጋሉ፣ ለድንዛዜም ሰበብ ይሆናሉ። “መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ” የሚለውን ሃሳብ ገሸሽ ያደርጉታል (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡1)። ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴን ስለሚናፍቁ ብቻ የኃይልን መገለጥ ለማድነቅ ስለሚጓጉ ብቻ ያለ ምንም ምርመራ አንዱም እንዳይነካ ከጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ይከላከላሉ፣ ይጋርዳሉ፣ ለሰይጣን ስውርና አሳሳች አሠራር ከለላ ተገን ይሆናሉ። “ሁሉ ለማነጽ ይሁን፣ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ ሲረግጡ ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆኑ ይመስላቸዋል (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡ 37-40)። እነኚህ ሁለቱም አካሄዶች ሊታረሙ የሚገባ ጐጂ አካሄዶች ናቸው።
አንዳንዶች በቃሉ ከመኖር ይልቅ የቃሉ ጠበቆች፣ በመንፈስ ቅዱስ ከመመላለስ ይልቅ ለመንፈስ ቅዱስ የፀጋ ስጦታዎች ነገረ ፈጆችና ተሟጋቾች ለመሆን ይታጠቃሉ። በአንደበት ጠበቃ ለመሆን ከመነሳት ይልቅ በቃልና በተግባር ምስክር መሆኑ ዋናና ተፈላጊ ነገር ነው። "ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ይሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አመጸኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፣ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፣ ነገር ግን ከምድር ነው የሥጋም ነው የአጋንንት ነው፣ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ሥፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት። በኋላ ታራቂ ገር እሺ ባይ ምሕረትና በጐ ፍሬ የሞላባት ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል (ያዕቆብ 3፡ 13-18)።
“ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል” እንዲል ቃሉ (ምሳሌ 2፡11) በዚህ ጽሑፍ ዓይነተኛ የሐሰት አሠራር መልኰች ምን እንደሆኑና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ምን መሆን እንዳለባቸው የሚጠቁሙ አሳቦች ተሰንዝረዋል። የ”አዲስ ዘመን” እንቅስቃሴ (“ኒው ኤጅ”) ዘመናዊነትን የሥነ ልቡና ሳይንስን የጥንቆላ አሠራርን የሩቅ ምሥራቃውያንን አስተሳሰብና ፍልስፍናን በማጣመር አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመመስረት የሚጥር ሲሆን ለሐሰተኛው ክርስቶስ መምጣት ጥርጊያውን የሚያመቻች ሴራ ነው። ከመንፈስ ሙትነት እንዲሁም በራስ ከተዋጠ ግልብ መንፈሳዊ ሕይወት እግዚአብሔር ይጠብቀን! በጠራና በነጠረ የክርስትና ሕይወት ያመላልሰን፤ አሜን!!
የመጨረሻው ዘመን ወንጌል በዓለም ሁሉ የሚሰበክበት ሰይጣን የመጨረሻው ጊዜ መሆኑን አውቆ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ዓለምን ለጥፋት የሚያስከትትበት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳት በከፍተኛ ደረጃ በረቀቀ መንገድ የሚፈታተንበት ነው። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 እንደምንመለከተው ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው የመምጣቱንና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምን እንደሆነ ንገረን ብለው ጠየቁት። እርሱም ሲመልስላቸው “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ” አላቸው። ጦርንም የጦርንም ወሬ እንደሚሰሙ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሳ፣ ራብም ቸነፈርም የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ሥፍራ እንደሚሆን እነዚህም እንደ ምጥ ጣር መጀመሪያ እንደሚሆኑ ነገራቸው። ለመከራ አልፎ መሰጠት፣ መገደል፣ ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መጠላት፣ ብዙዎችም እንደሚሰናከሉና እርስ በርስ አልፎ እንደሚሰጣጡ፣ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት እንደሚነሱና ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፣ ከዓመፃ ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ፣ ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት

