ከፒኤችዲ እስከ ጠቅላይ

እንግሊዛዊው ፕሮፌሰር አሌክስ ድ ዋል የተፍትስ ዩኒቨርሲቲ (አሜሪካ) ፒስ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ነው። “Plagiarism in Abiy Ahmed’s PhD Thesis: How will Addis Ababa University handle this?” የሚል ጽሑፍ በፈረንጆች ኤፕሪል 22/2023 ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ገጽ ላይ አትሟል። “Abiy Ahmed—PhD?” ብሎ ሜይ 4, 2022 ከፃፈው የቀጠለ ነው።

የአሌክስ ክስ፦ 1/ የጠ/ሚ ዐቢይ ፒኤችዲ ማሟያ ጽሑፍ 62 በመቶ ከሌሎች ሠነዶች (ቃል በቃል) የተኮረጀ/የተሠረቀ ነው (ኩረጃን በሚያጣራ ሶፍትዌር ውጤቱ ተያይዟል) 2/ በ26 ወር ውስጥ፣ ለዚያውም በትርፍ ጊዜ ፒኤቺዲን ያክል ማጠናቀቅ በተኣምር ካልሆነ አይቻልም (አግባብነት ያለው ጥያቄ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ወጥ የሆነ መተዳደሪያ አላቸው ማለት አይደለም) 3/ ዐቢይ ጥናታቸውን በዳኞች ፊት ባቀረቡበት እለት ሽመልስ አብዲሳ (የአሁኑ የኦሮምያ ፕሬዚደንት)፣ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ጄኔራል አባ ዱላ ገመዳ እና የፀጥታ ሰዎች መገኘታቸው በአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ዳኞች ላይ ተጽእኖ አሳድሯል (የግምገማው ቪዲዮ ተያይዟል፤ ተጽእኖውን ማረጋገጥ ግን ይከብዳል)፣ ስለዚህ 5/ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ለዝናው እና የዓለም አቀፍ የምርምር መመዘኛዎችን ለማስከበር ሲል ለዐቢይ የሰጠውን ፒኤችዲ መሠረዝ አለበት የሚል ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ዐቢይ የመጀመሪያ ድግሪ መቸና ከየት ተቀበሉ? ይኸ ሳይጣራ እንዴት ወደ ፒኤችዲ ተሸጋገሩ የሚሉ አሉ።

ተገቢ ጥያቄ ነው። የዐቢይን ማሟያ ጥናት (“Social Capital and its Role in Traditional Conflict Resolution: The Case of Inter-religious Conflict in Jimma Zone of the Oromia Regional State in Ethiopia”) በጥሞና ላነበበ፣ ወጥነት እንደሌለው ያስታውቃል። መጀመሪያ ግን ዐቢይ ለተሠነዘረባቸው ክስ መልስ ሊሰጡበት ይገባል፤ ቀጥሎ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ። ያለፈቃድ የሌሎችን የአእምሮ ውጤት መኮረጅ በዓለም ዙሪያ እያስከተለ ስላለው የሕዝብ ደህንነትና የሥልጣን መዛባት ከ20 ዓመት በፊት በሌላ ሥፍራ ጽፌአለሁ። ለምሳሌ፣ በአሜሪካ ሆምላንድ ሴኪዩሪቲና በስቴት ዲፓርትመንት፣ ወዘተ፣ በተጭበረበረ ዲፕሎማ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ከተሾሙ በኋላ የተሰናበቱ ባለሥልጣናት ነበሩ።

መንገዱ ገለጥለጥ እንዲልልን ጥሻውን በቅድሚያ እንመንጥር? ሀ/ አሌክስ ድ ዋል ማነው? ይህንን ጉዳይ ለምን ተመላለሰበት? በሌላ ሥፍራ፣ ዐቢይ ጴንጤቆስጥያዊ አማኝ እንደ ሆኑ፣ እምነታቸውን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋላቸውን (እውነት ነው) በከሃዲ ብዕሩ ቃኝቶ ነበር፤ ለ/ አሌክስ በሌሎች በእነማን ላይ ተመሳሳይ ክትትልና ትችት አካሂዷል? እግረ መንገድ ስለ አሌክስ የምናውቀውን ጥቂት እንዘርዝር፡ 1/ አሌክስ በጎልማሳነቱ (ዛሬ ዕድሜው ስድሳ ዓመት ነው) በግራ ዘመም ፖለቲካና በትጥቅ ትግል ፍቅር በመወሰዱ ከእነ መለስ ጋር 40 ዓመት የዘለቀ ቁርኝት ሊፈጥር ችሏል። አሌክስ በፈረንጆች 1984 ዳርፉር ሱዳን እንደ እኛው አገር ረሓብ ገብቶ ነበረና፣ ለሶሻል አንትሮፖሎጂ ዶክትሬት ማሟያ ምርምር ሱዳን አገር መጥቶ ነበር። መለስን “ጓድ መለስ” ብሎ ይጠራቸው ነበር፤ አዲሳባ በመጣ ቁጥር መለስን/ህወሓት ባለሥልጣናትን ይገናኝ ነበር 2/ አሌክስ የመለስ ፋውንዴሽ መሥራች ቦርድ አባል ነው 3/ መለስ ዜናዊ፣ ኤራስመስ ዩኒቨርሲቲ (ዘ ኔዘርላንድስ) በመላላክ ለጀመሩት የማስተርስ ፕሮግራም African Development: Dead Ends and New Beginnings የተሰኘ ጥናት ሳያገባድዱ በፈረንጆች 2012 ሞተዋል። አሌክስ በ2013 በአፍሪካን አፌርስ መጽሔት ላይ The theory and practice of Meles Zenawi ብሎ አድሎአዊነት የሚታይበትን ሐተታ አሳትሟል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ ኖሯቸው ከፍተኛ ዲግሪ ስለ ጫኑ የህወሓት ባለሥልጣናት ግን ትንፍሽ አላለም። (የአሌክስን የተንጋደደ አካሄድ ለመጠቆም እንጂ በዐቢይ ሠነድ ላይ ጥያቄ ማንሳቱን ለመከራከር አይደለም፤ ወይም የመለስን ከፍተኛ ምሑራዊ አቅም ከዐቢይ ጋር ለማነፃፀር አይደለም!) 4/ አሌክስ ህወሓትን መደገፍ ብቻ ሳይሆን በፊታውራሪነት፣ “ህወሓት ዳዊት፣ ጎልያዱን የኢትዮጵያን መንግሥት ድል አደረገ” የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ሲያካሄድ የኖረ ግለ ሰብ ነው። አናሳው በደለኛ ሊሆን እንደሚችል አልገደደውም። ኖቬምበር 2020 ጦርነት እንደተቀሰቀሰ አሌክስ ከአሜሪካ፣ አጋሩ ታጋይ ሙሉጌታ ገ/ህይወት ከመቀለ የህወሓትን ድልና ተፈጸመ ያሉትን ጄኖሳይድ ሌት ተቀን ለዓለም ያሠራጩ ነበር 5/ አሌክስ፣ ስለ ዐቢይ ፒኤችዲ ባተመው ሁለተኛ ጽሑፉ ላይ፣ ተባባሪዎቹ ያን ኒሰን፣ ገ/ክ ገ/ሥላሴ፣ ቡድ ሩክማ እና ሩንዳሳ እሸቴ ናቸው። ገ/ክ ገ/ሥላሴ የትግሃት (ከአገር ውጭ በየትምህርት ተቋማት የሚገኙ ትግራዋይ አክቲቪስቶች) መጽሔት መሥራችና ዋና አዘጋጅ ነው፤ መጽሔቱ የተጀመረው ኖቬምበር 2020 (በሰሜን እዝ ጦር ሠፈር፣ በማይካድራ፣ በትግራይ ጦርነት እንደ ተጀመረ ማለት ነው)። ያን ኒሰን፣ ቡድ ሩክማ እንደ አሌክስ ድ ዋል፣ እንደ ማርትን ፕላውት፣ ትሮንቮል፣ ቲም ቫንደን፣ ወዘተ የህወሓት ጥብቅ ወዳጆችና (በተለይ አማራ ጠልና) የኢትዮጵያን በየክልል መበጣጠቅ እውን ለማድረግ የሚተጉ አውሮጳውያን ናቸው።

በዚሁ ሁለተኛ ጽሑፉ መግቢያ ላይ አሌክስ፣ ዐቢይ ዶክትሬት ከተቀበሉበት ከ2017 አንስቶ የጥናታቸው መ-ኮ-ረጅ ጉዳይ ሲወራ ሰንብቶ፣ ይፋ የወጣው በሩንዳሳ እሸቴ ነው ይለናል። ሩንዳሳን የጠቆመን፣ ግለ ሰቡ ኦሮሞ ስለ ሆነ፣ ሌሎች ተባባሪዎቹ ትግራዋይና ደጋፊዎች መሆናቸውን ለመሸሸግ ይመስላል። በጽሑፉ ግርጌ የራሱንና የሌሎችን ሲጠቅስ፣ የሩንዳሳን ስም እና ብቃት ሳይጠቅስ አልፎታል 6/ አሌክስ ከአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ ኤንድ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ ተቋም (IPSS) ቁርኝት ነበረው፤ እየተመላለሰ ንግግር ያደርግ ነበር። ተቋሙን በአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ሥር በፈረንጆች 2007 ያቋቋመው ህወሓት ነው። ዓላማው ህወሓትን ከሽብርተኛ ገጽታው አላቅቆ ሰላምና ልማት አራማጅነቱን ለማስተዋወቅ ነው። IPSS ከመነሻው አሌክስ ከሚመራው ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን (ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ) ጋር ትሥሥር ነበረው። መሥራቹ የህወሓት ታጋይና ከፍተኛ አባል ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት ነው። ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት IPSSን ካቋቋመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከአሌክስ ጋር ለመሥራት ወደ ተፍትስ አሜሪካ ተጉዟል፤ በዚያም የተለያዩ ትግራዋይን በምርምር አሳትፏል፤ የህወሓትን አቋም ዋሺንግተን ዲሲ ለሚገኙ ኃይላት አቀብሏል። አካሄዱ ባጭሩ የህወሓትን አርቆ ማየት ይጠቁመናል።

ዐቢይ፣ ምሑራዊ ገጽታን የተላበሱ ንግግሮች እንደሚያደርጉ ከማንም የተሠወረ አይደለም። መለስ ዜናዊ ምሳሌአቸው እንደ ሆኑ ከዚህ ቀደም ነግረውናል። ሥልጣን እንደ ተረከቡ፣ ካቢኔአቸውን፣ የፓርላማ አባላትን ሰብስበው ስለ አስተዳደር/አመራር/ ወዘተ ሲያስተምሩ ደጋግመው በቴሌቪዥን ታይተዋል። የመለስ ተጽእኖ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ዐቢይ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ባለ-3 ቅጽ “መደመር” መጽሐፎችን (በአማርኛ በኦሮምኛ በእንግሊዝኛ፤ በድምጽ ንባብ ጭምር)፣ እርካብና መንበር፣ ፍሬ ከናፍርት ዘ ዐቢይ አሕመድ (እንደ ንጉሡ አፄ ኃይለሥላሴ) አሳትመው አሠራጭተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልልቅ የእንግሊዝኛ ቃላትን በንግግራቸው መሓል ጣልቃ ማስገባት ጀምረዋል (የተሾሙ ሰሞን ካሰሟቸው ንግግሮች ጋር አነፃፅሩ)። በየበዓላቱ ረጃጅም ጽሑፎችን በፌስቡክ በትዊተር መለጠፋቸው፣ ከኃይማኖት እስከ ስነ ጽሑፍ፣ እርሻ ልማት፣ ፍልስፍና እስከ ኅዋው፣ ሚሊቴሪና ፖለቲካ ሳይንስ፣ የአየር ጠባይ፣ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ትምህርት ፖሊሲ፣ ህገ መንግሥት ወዘተ አስተያየትና አመራር ሲሰጡ ይደመጣሉ። የህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ሙሌት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የተጠራቀመው ኲሬ ለዓሳ እርባታ እና ለቱሪዝም አመቺ እንደ ሆነ ነግረውናል። በወቅቱ የተደረገ ጥናት ግን የለም።

ስለ ሰላምና ሴኪዩሪቲ ኢንስቲትዩት (IPSS) አመሠራረት ከላይ ጠቁመናል። ህወሓት የሚታወቀው፣ በጎሣ ፌዴራሊዝም፣ በ “ፈጣን” ኢኮኖሚ እድገት፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ዲሞክራዊያዊ አስተዳደርን በመንፈግ፣ ከህግ ይልቅ መሳሪያ በማንሳት ነው። ያንን ገጽታ፣ ሽበት መደበቂያ ጥቁር ቀለም እንደሚቀቡ ባለሥልጣኖች፣ በሰላም፣ በልማትና ሴኪዩሪቲ ለመለወጥ አልሞ ነው። ህወሓት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ አመራር ነበረው። IPSSን በአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሲያቋቁም ከማንም ፈቃድ መጠየቅ አላስፈለገውም፤ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መፋለሳቸው አልገደደውም። የዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴርን አመራር ለፖለቲካው ማሳኪያ አውሎአቸው ነበር። “የክብር ዶክትሬት” አሠጣጥ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። IPSS ከተቋቋመበት ከ2007 ጀምሮ፣ የምሩቃንን ስም ዝርዝር፣ የምርምር ጥራትና የመግቢያ ብቃት ዝቅተኛነትን መመልከት፣ ተቋሙ የህወሓትን ሥራ ለሚሠሩ ማካካሻ መደረጉ ያስታውቃል፤ (ማእረጉ ለመሾምያ፣ ክፍያው ከመንግሥት ካዝና ሆኖ)።

ዐቢይ፣ ከህወሓት ጋር የኖሩ፣ የህወሓትን ሥራ በታማኝነት ሲሠሩ የኖሩ ናቸው። መለስ ዜናዊ ከኤርትራ ጋር በተደረገው የ1998ቱ ጦርነት ጦሩ ወደ ኤርትራ መገሥገሥ ሲጀምር እንዳስቆሙ ሁሉ፣ ዐቢይም በትግራይ ዘመቻ ሰሞን ያንኑ ዱካ ተከትለዋል። ባጭሩ፣ የዐቢይ ፒኤችዲ የህወሓት ዘመን አሠራር አንድ ገጽታ ነው፤ በ IPSS እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስም የተፈፀመውን ላጤነ፣ ትውልድ አጥፊ ተግባር እንደ ነበረ አያጠራጥርም።

አሌክስ ወዳነሳው ጥያቄ እንመለስ፦ የመጀመሪያ ጽሑፉ፣ ዐቢይ ብሎ ፒኤችዲ! የሚል ነው፤ ሁለተኛው፣ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ክብሩን ለማስጠበቅ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ሳይውል ሳያድር ይንገረን! ነው። አሌክስ የህወሓት አፈቀላጤ እንደ ሆነ አይተናል። ምሑር ቢሆንም፣ ምሑርነቱ በህወሓት የትጥቅ ትግል ላይ ስለ ተመሠረተ፣ ከእውነቱ ይልቅ የህወሓትን ጀግንነት ማውሳት ሲቀናው ይታያል። የቀጠረውን ተቋም (ፒስ ፋውንዴሽን) አገልግሎቶች ለመወገኛ ማዋሉ አካዴሚያዊ ሥነ ምግባር ያፋለሰ ድርጊት ነው። በአንፃሩ፣ በትግራይ ለተነሳሳው ግጭት፣ ጠ/ሚ ዐቢይ ያሰሟቸው ጥንቃቄ የጎደላቸው አገላለፆች (በዱቄት፣ በአጋንንት)፣ የአሌክስ ድርጊት በቀላል እንዲታለፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል።

ዐቢይ የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ተደርገዋል። ለዚህ አፃፋው፣ ከህወሓት ጋር በኖሩባቸው ዘመናት የተከማቹ ማዋረጃ ሰነዶችን ይፋ ማውጣት ነው። ዐቢይ የተሸለሙት የሰላም ኖቤል ይመለስ ማለት የመጣው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው። በአሌክስ ቤት፣ የህወሓትን ክብር ለማስመለስ በብዕር ትጥቅ ትግል መዋደቁ ነው።

የዐቢይ ፒኤችዲ ጥናታዊ ጽሑፍ አሌክስም እንዳመለከተን ያለጥርጥር እንከን አለበት። ዐቢይ ብቻ አይደሉም፤ አገር ሁሉ ተነካክቷል ብሎ ማለፍ ይቻላል፤ ይኸ አካሄድ ግን የጥናቱ ሰነድ መኮ-ረጅን ሊያስተባብል አይችልም! (አሌክስን)፦ አንተው በካድሬነት ያገለገልከው ህወሓት የፈጠረውና የፈፀመው ስህተት ነው ማለት ይቻላል፤ ይህ ግን የጎደፈውን የአዲሳባ ዩኒቨርሲቲን ክብር አያስመልስም! ለማንኛውም፣ ህወሓትን ብቻ መኮነን አግባብ አይደለም፤ ግለ ሰቦች በየትም አገር ሳይገደዱ በየትም መንገድ ማእረጉን ይፈልጉታልና! ወጪ ከመንግሥት ካዝና ሆኖ፣ በሊደርሽፕ ማስትሬት የተቀበሉ ሹማምንት ይታወሱናል፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ያላጠናቀቁ ነበሩባቸው። ሆኖም፣ እንደ ድግሪ አበዛዝ ሳይሆን፣ የአገር አስተዳደር ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖብናል።

ባለፈው ወር የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በተጨማሪ የአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር እንዲሆኑ ተሹመዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ መማክርት ሰብሳቢ ተደርገዋል። ከጠ/ሚ ዐቢይ ፒኤችዲ ጋር በተያያዘ ምን መፍትሔ ሊያመጡ ይሆን? ወይስ ሹመቱ አጋጣሚ ነው?

ሌላ ጥያቄ እንጠይቅ፦ በማእረግ፣ ጠቅላይ ወይስ ፒኤችዲ ይበልጣል? ጠ/ሚ ወይስ ዶ/ር? ይህንን ለመመለስ ከብልኃተኛው መለስ ዜናዊ መማር ይጠቅማል፦ መለስ፣ በፈረንጆች 2002 ከደቡብ ኮሪያው ክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ ሐናም፣ በፖለቲካ ሳይንስ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም፣ “ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር መለስ ዜናዊ” ሳይባሉበት ከካዝና ውስጥ ሳይወጣ በፈረንጆች 2012 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አንድ ነገር ግልጽ ነው፦ አገር መምራት ፒኤችዲ መጫን አይጠይቅም። በምድራችን ፒኤችዲ (ዶ/ር) ማእረግ በጫነ ሹም ላይ (በተለይ በትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤት ቅጥረኞች ላይ) ምርመራ ቢካሄድ፣ ብዙዎች እንደ ጌታ ቀን እርቃናቸውን በቀሩ ነበር! የወንጌል አገልጋዮች ሳይቀሩ፣ ወንጌላዊ መባል አንሶባቸው (ወይም አርጅቶባቸው)፣ ባልተመረመረ ዶክትሬት፦ ክቡር ዶ/ር ቄስ (ክቡር ዶ/ር መጋቢ፤ ክቡር ዶ/ር ፓስተር) መባልን ሲመርጡ ማየት፣ ዘመኑ እውነትም የክህደትና የቅጥፈት ነው ያሰኛል!

~ ምትኩ አዲሱ

© September 2023 by Mitiku Adisu. All rights are reserved.

ኅብር ሕይወቴ| የማርያም ታላቅ አእምሮከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ