ግምገማ

ጥበቡ፣ የምድረበዳው እረኛ

በሊሻን አጎናፍር፤ 4ኛ እትም / ሚያዝያ 2006 ..፣ ርኆቦት አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፤ 396 ገጽ፤ ዋጋው፦ 150 ብር/ 20 ዶላር

drTibebuBk

"የዶክተር ጥበቡ ኃይለሥላሴ የሕይወት ታሪክ" በባለቤቱ በወ/ሮ ሊሻን አጎናፍር ተጽፎ ዶ/ር ጥበቡ ባረፈ በዓመቱ ነሐሴ 2005 ዓ.ም. መጀመሪያ ታተመ፤ ይኸ አራተኛው እትም ነው። በመጀመሪያው እትም ውስጥ የሌሉ ሰነዶችና ፎቶግራፎች በአራተኛው ውስጥ ተካትተዋል። ሽፋኑና የፊደላቱ አቀራረጽ ያምራል። መጽሐፉ በአንድ ቦታ ሁኔታና ዘመን የተካለለ ባለመሆኑ፣ ላላነበቡ ታሪኩ ሳይዛነፍ ማስረዳት ይቸግራል። አዲስ አበባ ብሎ ሶማልያ፣ ኢራቅ ብሎ እስራኤል፣ ወዘተ። የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ጠቅሶ ደርግና አሁን የሚገዛውን። የሶሻሊስቶችና የካፒታሊስቶች የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን። የድንበርየለሾችና አናሳ ኃያላን ዘመን። ቤተክርስቲያን በጽኑ መከራ ውስጥና በ"ነጻነት" ዘመን። በምርኮና በስደት። ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ያልተለወጠውና ጸንቶ የዘለቀው የዶ/ር ጥበቡ በመከራና በደስታ የክርስቶስን ፈለግ መከተልና እግዚአብሔር አሰባስቦ ያጸናው ትዳራቸው ነው።

የምድረበዳው እረኛን ለማንበብ በቅድሚያ ሁለት ጉዳዮችን ማጤን ያሻል። በመጀመሪያ፣ የዶ/ር ጥበቡ ታሪክ የተራኪዋ የባለቤቱ የወ/ሮ ሊሻን፣ የቤተሰቦቻቸውና የቤተክርስቲያን ታሪክ መሆኑን፤ ቀጥሎ፣ መጽሐፉ ዶ/ር ጥበቡ ባረፈ ዓመት መገባደዱ ለተራኪዋ ኀዘን ማፍሰሻ አሸንዳ መሆኑን፤ ባጭሩ፣ ከባለታሪኮቹ ጋር ያልተሳሰረ ገለልተኛ ሰው አቅዶ የዶ/ር ጥበቡን ግለ-ታሪክ ከመሠረቱ ለመጻፍ በሚያደርገው ዝግጅትና አቀራረብ እንዳልተጻፈ መገንዘብ ያሻል። እነዚህን ነጥቦች ሳያጤኑ መጽሐፉን የሚያነብቡ ዶ/ር ጥበቡንና ትዳራቸውን እንከንየለሽ አስመሰሉት የሚል ጥርጣሬ ቢያድርባቸው አይደንቅም፤ መጽሐፉ ግን የተጻፈው በዚህ አሳብ አይደለም። መጽሐፉ የተጻፈው "ታላቁ እግዚአብሔር በአንድ ሰው ሕይወት ብሎም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሲገባ ሊሠራ ስለሚችለውና ስለሚያስችለው አስደናቂና መለኮታዊ ታሪክ ለማውሳት ነው።" [ከመግቢያው]

አብያተክርስቲያናት ለመጽሐፉ ያሳዩት አቀባበል የሚደነቅ ነው። [ከምስጋናው] ይህ የሚያመለክተው ሀ/ ታሪኩ ተነባቢ መሆኑን ለ/ ዶ/ር ጥበቡና ወ/ሮ ሊሻን በአብያተክርስቲያናት መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው መ/ ካፈራቸው የእድሜ-ልክ ወዳጆቹና ካገለገላቸው ብዙኃን አንጻር ዶ/ር ጥበቡን በአንድ ክልል መወሰን አለመቻሉን ነው። ቀብሪ ደሃር በምትባል ትንሽ ቀበሌ ኋላም በምርኮና በመረሳት ካምፕ ለአምላኩና ለሰው ልጅ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጣ፤ የታመነው አምላኩም በብዙ ከተሞች ላይ ሾመው። "የምድረበዳው እረኛ" መባሉ ለዚሁ ይመስለናል። በግብጽ ጥበብ የሠለጠነ ሙሴ ሕዝብን እንዲመራ በቅድሚያ የበግ ጠባቂ መሆን ነበረበት!

በዘመናችን የማያሳፍሩ የክርስቶስ ምስክሮች እንዳሉ መመልከት ተስፋ ሰጭ ነው። ቁጥራቸው ግን ለምን ተመናመነ? ወይስ እግዚአብሔር ላስፈላጊ ሰዓት በድብቅ ያስቀመጣቸው አሉ እንበል? ቆም ብለን ራሳችንንና አካባቢያችንን ለመመርመር እንገደዳለን። የሚችሉ ሁሉ መጽሐፉን ይግዙ፣ ያንብቡ።

በመጽሐፉ አጻጻፍና ሕትመት ላይ የብዙ ሰዎች አስተዋጽዖ ተዘርዝሯል። ደራሲዋ "የረሳሁት፣ ያጋነንኩት ወይንም ያልሆነ ታሪክ የዘገብኩት ካለ መርምሩልኝ" [ከምስጋናው] ማለቷና ለመጽሐፉ ጥራት የሚጠቅሙ አስተያየቶችን ከጅምሩ ለመቀበል መፍቀዷ ትሕትና ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄና ብልህነት ነው። ለምሳሌ፣ "አዲስ ትውልድ የአጻጻፍ ዘይቤዬንና ቋንቋዬን ይልቁንም መልእክቴን ይረዳልኝ እንደሁ እርግጠኛ ባልነበርኩበት ወቅት በኢትዮጵያ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሑፎቼን ያሳየሁት [ለምሕረት] ነበር። ረቂቁን አንብባና ለትውልድ አቻዎቿም አስነብባ፣ ኖኅ እንደላካት ርግብ መልካም ዜና ያመጣችልኝ ያበረታታችኝ … የኔው የድሮ አማርኛ ለዛሬዎቹ ወጣቶች አስተርጓሚ ያስፈልገው ይሆንን? የሚለው ስጋቴ በእሷ ተሻረልኝ።" [ከምስጋናው] በሌላ አነጋገር፣ ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው የጸሐፊው የአሳብ ርቀት ብቻ ሳይሆን የአንባቢው መረዳት ጭምር ነው። አዲሱ ትውልድና የቀደመው በመጠባበቅ ሲጓዙ ውበት አለው። በመመካከራቸው ሁለቱም ከአደጋ ይጠበቃሉ፤ የጌታም ስም አይነቀፍም። መጋቢ በቀለ ወልደኪዳን "ጣልቃ እየገባ" [2005 ዓ.ም.፣ ገጽ6] በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ይህንኑ የትውልድ ቅርርቦሽና ቅብብሎሽን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።

የምድረበዳው እረኛ ስለ አገልግሎት ክቡርነት፣ ስለ አገልጋይ ማንነትና፣ ወንጌል በቤተክርስቲያን ክልል እንደማይወሰን ምን ይጠቁመናል? ለነዚህ ጥያቄዎች አንባቢው የየራሱ ድምዳሜ ሊኖረው ይችላል። ሆኖም የሚከተሉት ጥቅሶች የዶ/ር ጥበቡንና የራሳችንን ሕይወት ለመቃኛ መነሻ የሚሆኑን ይመስለናል።

ሀ/ አገልግሎት ትሕትና እንጂ እልቅና አይደለም። "ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም ...፤" [ማቴ 20፡28] 

ለ/ አገልግሎት መቁረጥን፣ ጎራ መለየትን ይጠይቃል። "ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፣ ወይም አንዱን ይጠላል፣ ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል፣ ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም … ፤" [ማቴ 6፡24] 

መ/ ሊከብር የሚገባው አንድ ጌታ ብቻ ነው። "እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ … ፤" [ሉቃስ17፡10] 

ሠ/ ያለጸጋ አይሆንም፤ "እግዚአብሔር ጸጋን አብልጦ ይሰጣል ...፤" [ያዕ 4፡6-10] 

ኃያሉ እግዚአብሔር በእኔም እንኳ መሥራት ይችላል፤ በኔም ብቻ አይደለም በሌሎችም ይሠራል፤ ያለኔም መሥራት ይችላል ብሎ ማሰብ ምንኛ ማስተዋል፣ ምንኛ ዕረፍት ነው!

ከእንግዲህስ ምን ይደረግ? ዶክተር ጥበቡ ኃይለሥላሴ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ፣ አቶ መርኪና መጃ፣ አስቴር ጋኖ፣ ወዘተ የመሰሉ በቤተክርስቲያንና በአገር ደረጃ የሰጡትን አገልግሎት ትውልድ እንዳይረሳ ምን እርምጃ ይወሰድ? የሰሜን አሜሪካውያንን ታሪክ ስናገንን ጌታ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሰጣትን ስናሳንስ እንዳንገኝ ምን ጥንቃቄ ይወሰድ? ተስፋ የሚጣልባቸውን ወጣቶች ለማበረታታት የትምህርት፣ የሥልጠናና የኃላፊነት እድል በመስጠት ረገድ ምን ይደረግ? ዶ/ር ጥበቡ በሄደበት ሁሉ በመልካም ምግባሩና በሥራው የአገሩን ስም ማስጠራቱ በአገር ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው የአገር መሪዎች ጋር ማን ይነጋገር? በተለይ የሕክምና ባለሙያዎች በሚፈልሱበትና ከተማና ምቾት በሚሉበት ዘመን ሀ/ "ሁሉ ትላልቅ ከተማ ውስጥ ብቻ መሥራት የሚፈልግ ከሆነ ገጠሪቷ ኢትዮጵያ እንዴት ልትለማ ትችላለች? ለገጠሩስ ሕዝብ ከቶ ማን ሊደርስለት ይችላል?" [ገጽ130] ሲል ለነበረ፣ ለ/ ችግር ሸሽቼ ኃላፊነቴን ጥዬ አልሄድም ላለ መንግሥት ምን ያድርግለት?

በመጨረሻ፣ ዶ/ር ጥበቡና ወ/ሮ ሊሻን በየግዞታቸው ያሳለፉትን አስራ አንድ አመታት ቲዩረሰን የተሰኘ በስዊድንኛ እንዳሳተመው፣ ያም በኖርዌይ፣ በፈረንሳይ፣ በፊንላንድና በዴንማርክ አገራት ቋንቋዎች እንደ ተተረጎመ ተገልጿል። [ከመግቢያው] የምድረበዳው እረኛ በተራው ሲተረጎም መሠረታዊ ጉዳዮች እንዳይዘነጉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በቅድሚያ የሚተረጎምለትን አንባቢ የባህል፣ የፖለቲካ፣ የመልክዓ ምድር፣ የሃይማኖት ወዘተ አድማስ መገምገም ያሻል። ለምሳሌ፣ ባለ ታሪኩ የተወለደበትና ያደገበት ሥፍራ ሁሉ በካርታ መታየት ይኖርበታል። ሁለተኛ፣ የዘመን አቆጣጠር ወጥነት ቢኖረው ይመረጣል። ሦስተኛ፣ በተለይ ባህላዊ አስተሳሰቦችን፣ ፖለቲካዊ ሂደቶችን ለመግባቢያ ያህል ባጭሩ እንጂ ተራዝሞ ከዋነኛው ታሪክ እንዳያዘናጋ እንዳያሰለች መጠንቀቅ ያሻል። "ታላቁ እግዚአብሔር በአንድ [ፈጽሞ በተሰጠ] ሰው ሕይወት ብሎም በአንድ ቤተሰብ በኩል ሊሠራ ስለሚችለውና ስለሚያስችለው አስደናቂና መለኮታዊ ታሪክ" ማንበብ ምንኛ ደስ ያሰኛል! ለአገልግሎቱ ለሚሾም፣ ታማኝ አድርጎ ለሚያቆም፣ ኃይል ለሚሰጥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ለጌታችን ምስጋና ይሁን[1ኛጢሞ1፡12]!

የምድረበዳው እረኛን ለመግዛት ወይም ደራሲዋን ለማግኘት እዚህ ይጫኑ www.tibebu.org

.........................................

ምትኩ አዲሱ

ታኅሳስ 2007..