የማርያም ታላቅ አእምሮ [THE GREAT MIND OF MARY]

ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ። 2005 ርኆቦት አታሚዎች፤ አ/አበባ። መሸጫ ዋጋ፦ ብር 30/ዶላር 10። ሐተታና ግምገማ። ጥር 2006።

dr.wodajeneh

ይህንን መጽሐፍ በተለያየ መረዳትና የእምነት ክፍል የሚገኙ እያነበቡት ነው። አንዳንዶች አንባቢዎች የተጻፈውን ያለ ጥያቄ የሚቀበሉ ናቸው። አንዳንዶች በጸሐፊው ማንነት ተገትተው ጥያቄ ማንሳት የማይደፍሩ ናቸው። ደራሲው ባልጠበቀው መንገድ የሚተረጉሙ አሉ። ደራሲው ባቀረባቸው ነጥቦች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ አሉ። የመጽሐፍ ተግባሩ ማነጋገሩ፣ ማስተማሩና ጥያቄ ማስነሳቱ ነው። የመነጋገሪያ ምክንያት ስለሆነን ደራሲው ሊመሰገን ይገባል። የደራሲ ሥራ ደግሞ አድካሚ ብቻ ሳይሆን የሚያስጠይቅም ነው፤ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም። ጠያቂና ተጠያቂ ይጠባበቃሉ፤ የሁለቱም ተጠሪነት ለእግዚአብሔርና ለሰው ነውና።  “ሐተታና ግምገማ” ያልንበት ምክንያቱ በመጽሐፉ ገጾች የተነሡት አሳቦች በሃይማኖት ብቻ፣ በፖለቲካ ብቻ፣ በስነ ጽሑፍ ብቻ፣ በስነ መለኮት ብቻ፣ በግለሰብ ማንነት ብቻ የሚወሰኑ ስላልሆነ፤ የሚቀሰቅሱትን አሳቦች ለማገናዘብ፣ ደራሲው ጀምሮ እልባት ያልሰጣቸውን፣ አገላለጹና አቀራረቡ አሻሚና አጠያያቂ የሆኑበትን ለመመርመር ነው፤ “መርምሩ” ተብለናል [1ኛ ዮሐንስ 4፡1]። ይህን ግምገማ በዚህ መንፈስ ያንብቡት። 

በመጽሐፉ ይዘትና ስነ መለኮታዊ አቀራረብ ዙሪያ ቃለ ምልልስ ለማድረግ ያደረግነው ሙከራ ባይሳካልንም፣ ወንድማችን ዶ/ር ወዳጄነህ እግዚአብሔር መጽሐፉን እየተጠቀመበት እንደ ሆነና በሁለተኛው እትም ላይ ስነ መለኮታዊ መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ዲሴምበር 23/2013 በኢሜይል አስታውቆናል። ከላይ እንደ ገለጽነው መጽሐፍ መጻፍ የግል ተግባር ቢሆንም የጋርዮሽ ገጽታም አለውና ምናልባት ለሁለተኛው እትም ቢያግዝ፣ ያዘጋጀነውን ሙሉ ሐተታ ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን፣ ትዝብቶቻችንን በከፊሉ እንደሚከተለው አስፍረናል።

“የማርያም ታላቅ አእምሮ” 122 ገጾች ሲኖሩት፤ ከሁለት እስከ አራት ገጾች በሚያህሉ አርባ ምዕራፎች ተከፋፍሏል። ደራሲው፣ የማርያም ማንነት እንደ አያሌ የታሪክ ሰዎች "አከራካሪ" ነው ሲል ይጀምራል። ቅድስት ማርያም ከኢየሱስ ሌላ ልጆች ነበሯት? አምልኮ ይገባታል? በሚሉ ነጥቦች ላይ መለያየት መኖሩን ገልጾ፤ መቻቻል እንዲኖር እርስ በርስ መነጋገርና በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያሻል የሚል በጎ አሳብ ሠንዝሯል። ይህ የደራሲው ዓላማ ምን ያህል ተሳክቶለታል? እስቲ ጉልህና ተጓዳኝ ትዝብቶችን እናስቀድም፦

1/ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ/ስነ መለኮታዊ ትንታኔ ይልቅ ከራሱና ከሌሎች ልምድ በመነሳት መልካካም ምክር አዘል አባባሎችን ማቅረብን መርጧል [“ኢየሱስን የቅርብ ወዳጅዎ ያድርጉት” ገጽ 37፤ “ቃሉን በማንበብ የሚወስዱት ጊዜ ኪሳራ አይሆንብዎትም” ገጽ 76፤ ወዘተ] 2/ “የጥበብ ዕንቁ” ብሎ በሰየማቸው በነዚሁ 40 ምዕራፎች “ከማርያም የሕይወት ምሳሌነት ምን ያህል ተምረናል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥሯል። 3/ “በዚህ መጽሐፍ የእርስዎን እምነት የሚያጣጥል ወይም የሚቃወም አንድም ነገር አያገኙበትም … ምክንያቱም … ሃይማኖታችንን ለማሳመር የሚጠቅሙ ቁም ነገሮች እንጂ የዶክትሪን ጉዳዮች አይደሉም” በማለት አንባቢውን ለማረጋጋት ሞክሯል [ገጽ 6-7]። “ዶክትሪን” ሲል ምን ማለቱ እንደ ሆነ ግን አላብራራም፤ ስላላብራራ ዶክትሪን ሃይማኖታችንን ለማሳመር አይጠቅምም የሚል አስመስሎበታል። 4/ የፊደላቱና የመጽሐፉ ሽፋን ጎበዝ ባለ እጅ እንደ ሠራቸው ያመለክታሉ። የፊደላት ግድፈት እምብዛም አይታይም፤ በተለይ በወንጌላውያን ጸሐፊዎች በሚታተሙ መጽሐፍት ግድፈት የተለመደ ቢሆንም፣ ጥራት ያላቸውም እንዳሉ ማየት ተስፋ ሰጭ ነው። 5/ ማርያም እንደ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ልድያ፣ ዮሐንስ፣ ሉቃስ ወዘተ ከተሰጣት ጸጋ ውጭ የምትታወቅበት የሰፋ ግለ-ታሪክ የላትም [ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰቦቿ አልነገረንም]። እርግጥ አፈ-ታሪክ አለ፤ አፈ-ታሪክ ግን እርስዋ ከሞተች በኋላ ከማህጸኗ ስለ ተገኘው አዳኝ ማንነት የአንዱን አንጃ አስተምህሮ ለማገዝ የተቀናበረ እንጂ ሙሉ በሙሉ በታሪክ መረጃ የተደገፈ ነው ማለት አይደለም። ከጥንት የነበረ ነው ማለት ደግሞ አንድን ትምህርት እውነት እንደማያደርገው አንርሳ። በወንጌላት ከተጠቀሰው ብንነሳ ቅድስት ማርያም የምትታወቀው “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” በመባሏ [ሉቃስ 1፡28፣42]፤ “እነሆኝ የጌታ ባርያ” በማለቷ። ገብርኤል የነገራትን፤ ከእረኞች፣ ከሰብዓ ሰገል፣ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከነበሩት ከስምዖንና ከሐና፣ በስተርጅና ከፀነሰችው ከዘመዷ ከኤልሳቤጥ የተነገራትን ሁሉ በልብዋ እየጠበቀች በማሰላሰሏና ሃሴት በማድረጓ ነው፦ ["ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፣ ሉቃስ 1፡47። ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር ... ሉቃስ 2:19፣51"]

በብሉይና በሐዲስ ቃል አገባብ “ልብ” እና “አእምሮ” ተመሳሳይ ናቸው እንኳ ቢባል፣ ወንድማችን ዶ/ር ወዳጄነህ ለምን በማርያም “አእምሮ” ላይ እንዳተኮረ አላብራራልንም። “አእምሮዋ ታላቅ” ስለ ተባለላት አቢጊያ ስለምትባል ሴት [2ኛ ነገሥት 4፡8፤ 1ኛ ሳሙኤል 25፡3] በመጥቀስ፤ “እንግዲህ የአቢጊያ አእምሮ ‘ታላቅ’ ከተባለ ከአቢጊያ በብዙ የምትበልጠው የቅድስት ማርያም አእምሮ “ታላቅ” ቢባል ማን ‘ይበዛባታል’ ይላል?” ብሎናል [ገጽ 7]። ጉዳዩ “ታላቅ” ከሚለው ቃል ላይ ይመስላል። በሌላ አነጋገር፣ ማርያምን በ “ታላቅ አእምሮዋ” ለማሳየት “ታላቅ አእምሮ” አላት የተባለላትን ሌላ ሴት ዋስ መጥራት ነበረበት። ማወዳደርና ማበላለጥስ ያስፈልግ ነበር? ሌላው ጉዳይ፣ “ታላቅ አእምሮ” በአገባቡ አስተዋይነትና ጠንቃቃነትን አመልካች መሆኑ ነው፤ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል” እንዲል [ምሳሌ 2፡11። በተጨማሪ 1 ሳሙ 25፡ 33]። ደራሲው በሌላ ሥፍራ አንድ ሰው በአእምሮ ልቆ ሳለ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ግን ማስተዋል የጎደለው ሥራ ሊሠራ ይችላል ብሎናል፣ ገጽ 33]። ይልቅ የአቢጊያ ባል ናባል “ባለጌ፣ ግብሩም ክፉ” መባሉ የአቢጊያን አድራጎትና ማንነት ይበልጥ በገለጸው [1ኛ ሳሙኤል 25፡3]

 

*  *  *  *

የታሪኩን መነሻ ባንረሳ፦ ዳዊትን ንጉሥ ሳዖል አሳድዶት በምድረ በዳ ይኖር ነበር። ዳዊትና ሎሌዎቹ የናባልን እረኞችና ከብቶችን ከወሮበሎች ይከላከሉላቸው ነበር እንጂ አይነኳቸውም ነበር። ለምግብ የሚሆነንን ላክልን ብሎ ዳዊት በሥርዓት ላከበት፤ ናባል ግን መልእክተኞቹን ሰድቦና አዋርዶ መለሳቸው። ይህም ዳዊትን አስከፋው፣ እጅግ አስቆጣው። ሊያጠፋቸው እየመጣ እንደ ሆነ ስትሰማ የናባል ሚስት አቢግያ ፈጥና ስንቅ አስጭና ደረሰች። በስጦታዋ፣ በአንደበቷና በውበቷ ዳዊትን አብርዳ ማረከች፦ “በዚህ በምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጥል … እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤” ቀጥላ፣ “እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ ባሪያህን አስብ” አለች። ወደ ቤቷ ስትመለስ ናባል “እጅግ ሰክሮ” ነበር፤ በነጋታው ስካሩ ሲያልፍለት የሆነውን ነገረችው፣ “ልቡ በውስጡ እንደ ድንጋይ ሆነ” ከአስር ቀን በኋላም ሞተ። ባሏ በሕይወት እያለ ዳዊትን “አስበኝ” ማለቷ ኋላ ለመጋባታቸው ምን አስተዋጽዖ ነበረው? [1ሳሙ 25፡23-31]

6/ ሌላው ጉዳይ ዘመኑና የተገኘበት ማህበረሰብ በግለሰብ ላይ፣ ግለሰብም በማህበረሰብ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ጉዳይ ነው። ከተጽዕኖ ነጻ የሆነ ማንም የለም። “ታላቅነት”ን የሚያውጁ ቃላት በዚህ ዘመን ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ለዚህ በቂ ማስረጃ ይሆነናል። “ታላቁ” ግድብ። “ታላቁ” መሪ። “ታላቁ” አትሌት። “የቴዲ አፍሮ የታላቅነት ምሥጢር፤” ወዘተ። “ሌጀንድ” ደግሞ ለዘፋኞችና ለዘማሪያን ሲጠቀም ይስተዋላል። ጸሐፊያን የማህበረሰብ አካል ናቸውና አካባቢያቸው በነርሱ ላይ እነርሱም በአካባቢያቸው ላይ ተጽዕኖ አያደርጉም ማለት የማህበራዊ ኃይላትን አካሄድ አለመረዳት ነው። በዚህ ረገድ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት በቤተክርስቲያን መሪዎች የተንጸባረቁ አጠራሮችንና ማንነትን ለማበልጸግ የዕውቀት ገበያትን መድራት መመልከት በቂ ነው።

ዶ/ር ወዳጄነህን “ታላቅነት” ተጽዕኖ ሳያደርግበት አልቀረም [ምዕራፍ 40፤ “ራእይ፣ ሌጋሲ፣ ታላቅነት” ይላል]። ፕሬዚደንት ኦባማ፣ ቡሽ፣ ክሊንተን፣ አብርሃም ሊንከን፣ ሮዝቬልት፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ኦፕራ፣ ቢልጌትስ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ጸጋዬ ገ/መድህን፣ ሼህ አላሙዲ፣ ወዘተ ወዘተ የመሳሰሉ “ታላላቅ” ሰዎች ስም በየምዕራፉ መሰባጠር ይህን ድምዳሜ ግድ ይላል። መጽሐፉ ጥቂት የተማሩ ሰዎችን በማሰብ [ብዙሐኑን በመዘንጋት] የተጻፈም ይመስላል። ከመጽሐፉ 122 ገጾች ውስጥ በ101ዱ የእንግሊዝኛ ቃላትና ሐረጎች ይታዩባቸዋል። ይህ አንባቢን አለመለየት ነው። የኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት አማንያን ሁሉም እንግሊዝኛ ተናጋሪና አንባቢ ሆነዋል ካላልን በስተቀር። ይህ ሰሞነኛ ልማድ በቤተክርስቲያን ውስጥና ከቤተክርስቲያን ውጭ ባሉት መሪዎች ዘንድ ፈጥኖ መራባቱ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብና የባሕል ቀውስ ለመኖሩ ጠቋሚ ነው። ሕዝቡ ኢየሱስን "በደስታ" ይሰሙትና በትምህርቱ ይገረሙ የነበረው አገላለጹና ቋንቋው ተራውን ሕዝብ ይንቁ እንደ ነበሩት እንደ ሕግ መምህራኑ የተወሳሰበ ስላልነበረ [ዮሐ 7፡49፤ 9፡34]፣ ሕዝቡን በራሱ ቋንቋ ያነጋግር ስለ ነበረ፤ ከሚያውቁት ተነስቶ ወደማያውቁት ወደ ሰማያዊ እውነት ልባቸውን፣ ነፍሳቸውንና አእምሮአቸውን ያነሳ፣ ዐይናቸውን ይከፍትላቸው ስለ ነበረ ነው። [ስለ ሜዳ አበቦች ተናግሮ፣ ስለ ንጉሥ ሰለሞን ልብሰ መንግሥት። ስለ ወፎች ተናግሮ፣ ስለ እግዚአብሔር አባትነት፣ ወዘተ። [ማቴዎስ 6፤ ማርቆስ 12፡37፤ ማቴዎስ 7፡29፤ ማርቆስ 12፡37፤ ሉቃስ 24፡ 31፣ 32፣ 45]

“መንፈሳዊ” ቃላትን፣ በተለይ ከቤተክርስቲያን ውጭ ያሉትን ግራ የሚያጋቡ ቃላትን መጠቀም በጣሙን እየተለመደ መጥቷል። ይህን ጉዳይ በተለያዩ ወቅቶች ማንሳት ያበዛነው ወንጌል አገልጋዮች ሳያስተውሉ በአደራ የተሰጣቸውን መልእክት ሳያደርሱ መልእክቱ እንዳይጨናገፍ ወይም ያልተጻፈ ትርጉም እንዳይሰጠው በማሰብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ” [1ኛ ቆሮንቶስ 14፡19] ያለበት ምክንያቱ የአድማጭ የመረዳት አቅም ከተናጋሪው መምጠቅ ያላነሰ ግንዛቤና ኃላፊነት እንደሚጠይቅ ለማስረዳት ጭምር ነው። ጳውሎስ፣ በዘመኑ ዝነኛ ከነበረው ከመምህር ገማልያል እግር ሥር ሆኖ ትምህርቱን እንደ ተቀበለ ገልጿል [የሐዋርያት ሥራ 5፡34፤ 22፡3]፤ ከግሪክና ከዕብራይስጥ ዕውቀትና ባሕል ጋር በደንብ ይተዋወቅ ነበር። ሆኖም የተሰጠውን የወንጌል አደራ ለማዳረስ፣ ሊያስመካ የሚያስችል ዕውቀት እያለው፣ “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ... ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ፤ ሮሜ 1፡14፣ ቆላስይስ 4፡4” አለ።

ስለ አንድ ነገር ማወቅና ያንን ያወቁትን ሌላው በሚገባው መንገድ መግለጽ ለየቅል ናቸው። በዚህ ሚዛን፣ በመሪነት ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ በሚጽፉትና በሚያስተምሩት ከብዙሐኑ ማኅበረ ምዕመን በአስተሳሰብ የተራራቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። መሪ/አስተማሪ ለሚመራው/ለሚያስተምረው ዓላማን/ትምህርቱን ግልጽ አድርጎ የማቅረብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፤ አለዚያ መሪነት/አስተማሪነት አይገባውም። ዓላማን/ትምህርቱን እንደሚገባ አለማወቅ አለመደማመጥና ሁሉም በመሰለው መሄድን ያስከትላል። ለሚታየው ትርምስ፣ እውነቱን ለይቶ ላለማወቅ በጽድቅ ጉዳይ ግልጽ አቋም ላለመውሰድና ለአገልጋዮች ሥልጣን ማጣት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ዛሬ የሚደመጡ ስንት መሪዎች በቤተክርስቲያን አሉ? የብዙዎች አመራር በመሠረታዊ አስተምህሮዎች ዙሪያ ሳይሆን በማንነታቸውና በተከታዮቻቸው ብዛት ዙሪያ ተካሏል። የዚህ አሠራር አደገኛነቱ ግለሰቦቹ ሲሞቱ፣ በምክንያት ሲወገዱ ወይም ቀልብ የሚስብ አቀራረብ ያለው ሌላ ሲነሳ የምዕመን ግራ መጋባትና መበታተን ነው።

1/ አስር ሰዎች ስለ ማርያም ማንነት አስራ አንድ መልስ ሊኖራቸው ይችላል። ደራሲው ከመነሻው ስለ ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን አጭርና የማያሻማ ታሪክ በአንድ ገጽ ቢያሠፍር ኖሮ አንባቢው ከተጻፈው ውጭ ወደ ግምት እንዳይዛመት ማገጃ በሆነ። 2/ ምሳሌነትን በተመለከተ ማርያም፣ እንደ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” አላለችም [1ኛ ቆሮንቶስ 11፡1]። ሁሉም ግን ወደ ኢየሱስ ጠቁመው አለፉ። “እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና” [ዕብራውያን 12፡1-2]። በተቀደሰው ተራራ ላይ ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ ጋር ሲጸልይ ሙሴና ኤልያስ ተገልጠው አነጋገሩት [ማቴዎስ 17፡1-8]። ቀጥሎ፣ “ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም” ማለቱ የኢየሱስን መካከለኛነት የሚቀናቀን ሊኖር እንደማይገባ ለመግለጽ ነው። 3/ ገብርኤል ማርያምን፣ “ስሙን ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሲላት የሚወለደው አዳኝ መሆኑ ታውቆ ነው። እጮኛዋን ዮሴፍን፣ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል፤ ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” ሲለው አዳኝነቱ ለማርያምም ለዮሴፍም ጭምር ነው፤ “መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” [ሉቃስ 1፡31፣47፤ማቴዎስ 1፡21]። 4/ ወንድማችን ዶ/ር ወዳጄነህ በመጽሐፉ ላይ ላሠፈራቸው ዋነኛ አሳቦች ምንጫቸውን አልገለጸም። ደራሲው ከራሱ ያቀረባቸውና የተዋሳቸው አሳቦች ተነጣጥለው መቅረብ ይኖርባቸዋል። 5/ አራት ነጥብና ጥያቄ ምልክት [?።]፣ ድርብ ሠረዝና ቃለ አጋኖ [፤!] በብዛት መገኘታቸው ግድፈት ይሁን ታስቦበት ማወቅ አይቻልም።

 

*  *  *  *

የደራሲ/የመሪ ፈተናው የተረዳውን እውነት ለሌላ ማስረዳት መቻሉ ላይ ነው ብለናል። ደራሲ/መሪ ማስረዳት ካልቻለ ወይም ግራ ካጋባ ራሱም ከመነሻው አልተረዳም ማለት ነው። የሚቀጥለው እሑድ የሚሰበከውን ስብከት ካደመጡ በኋላ “ሰባኪው ምን ብሎ አስተማረ?” ብለው ራስዎንና ወዳጅዎን ይጠይቁ። እስቲ መልሱን በአንድ ትንፋሽ በአንድ ዓረፍተ ነገር ለመግለጽ ይሞክሩ። መሪዎች የሚያስተምሩትና የሚጽፉት ሁሉ በእግዚአብሔርና በሰው እንደሚያስጠይቃቸው በትህትናና በአጽንዖት ማሰብ ይኖርባቸዋል። በነዚህ ጥቂት ዓመታት በተለይ በወንጌላውያን የተጻፉ መጻሕፍትና ትምህርቶች ስለ ራስ ደጀን ሳይሆን ስለ ሮኪ ተራራዎች፣ ስለ ቀበና ወንዝ ሳይሆን ስለ ሚሲሲፒ፣ ስለ ግዕዝና ስለ ኦሮሚኛ ሳይሆን የፈረንጆችን ባሕላዊ ክርስትና ማጋዝና ማጉላት አብዝተዋል። የፈረንጆች ባሕላዊ ክርስትና የሰው ፊት ማየትና ማዝናናት ያበዛል። የእግዚአብሔርን ቃል ለማስረዳት እኒሁ በግዕዝ፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በዕብራይስጥና በግሪክ ባህልና ቋንቋ የተተረጎመውን ሳይሆን የእንግሊዝኛውን ያስቀድማሉ። በባሕልና በካርታ አቀማመጥ የተጎራበትናቸውን እስክንድርያ ግብጽን፣ ግሪክን፣ ኢየሩሳሌምን ዘልለው ዳላስና ኦክላሆማ አሜሪካ ይከርማሉ። እግዚአብሔር ከቋንቋ ሁሉ፣ ከነገድ ሁሉ የራሱ የሆነ ሕዝብ እንዳለው አንክድም። ከሌላው አንማርም አንልም፤ የምንለው የአድማጭን አቅም አንርሳ ነው። የራሳችንን ባናውቅና ብንንቅ ያልሆነውን ለመሆን ብንሯሯጥ ግን ለማያቋርጥ ግርግር እንዳረጋለን ማለት እንጂ። ሰው “በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና” [ምሳሌ23፡7]

ስለ ማርያም ስናስብ ዞሮ ዞሮ ከጥያቄ ማምለጥ አንችልም። ያም፣ ማርያም ስለ ራሷ ምን ብላለች? ስለ ኢየሱስስ? ኢየሱስ ስለ ራሱ፣ ሐዋርያቱም ስለ ኢየሱስ ምን ብለዋል? ከጥንት እስከ ዛሬ ቋሚ ችግር የሆነው የማርያም አለመግነን ሳይሆን በኦሮቶዶክስ፣ በካቶሊክ፣ በፕሮቴስታንት፣ በዓለም ባሉት ሁሉ ዘንድ የኢየሱስ አለመግነን ነው። “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” [1ጢሞቴዎስ 2፡5]። ኢየሱስ ዋነኛና መካከለኛ ሥፍራ ሲያገኝ ሁሉም ቦታ ቦታውን ይይዛል። “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” [ዮሐንስ 12፡32]። “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፣ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” [ዕብራውያን 7፡25]። “ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል” [2ቆሮንቶስ 3፡14-16]። “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና” [ቆላስይስ 1፡15-20]። “እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” [የሐዋ ሥራ 4፡11-12]

ሊታይ እንጂ ሊጋረድ የማይገባው እርሱ ብቻ ነው፤ “በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት” [ዮሐንስ 12፡20-22]። ከጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ጋር በተቀደሰው ተራራ ላይ ሲጸልይ ሙሴና ኤልያስ [ሕግና ነቢያትን ወክለው] በኢየሩሳሌም ስለሚጠብቀው መከራ ካነጋገሩት በኋላ ቀጥሎ ደቀ መዛሙርቱ ያዩት “ኢየሱስ ብቻ” ገንኖ አገልጋዮቹ መንገድ ለቀውለት ነበር። ሰማይ ተከፍቶ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት” ነው የተባልነው [ማቴዎስ 17፡5፤ ሉቃስ 3፡21-22]። በቅዱስ ተራራም ላይ “ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን” [2ጴጥሮስ 1፡17-18]። ዮሐንስ መጥምቁ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” አለ [ዮሐ 3፡30]። ማርያም፣ ኤልሳቤጥ፣ ክዋክብት፣ ሰብዓ ሰገል፣ እረኞች፣ስምዖን፣ መላእክት፣ የምድር ሥልጣናት፣ ወዘተ ሁላቸውም የኢየሱስን ጌትነት ነው ያበሰሩት።

ባጭሩ፣ በማርያም ማንነት ላይ ማተኮር አያስማማም፤ በዘመናት ሁሉ ተሞክሮ ያቃተ ጉዳይ ነው። ከአብ ጋር፣ ከራስ ጋርና እርስበርስ የሚያስማማ የተሰቀለውና ከሙታን የተነሳው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ብቻ ነው። ከላይ እንደ ጠቀስነው “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” አለ [ዮሐ 12፡32]። “አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና” [ኤፌ 2፡13-18]

 

*  *  *  *

maryzionስምምነት መፍጠር መልካም ነው። ለስምምነት ሲባል ግን እውነቱ እንዳይበረዝ ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ከላይ በሁሉ ዘንድ የሚታወቀውን የድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳን ይመልከቱ። ኢየሱስ የሚታየው መካከለኛ ሆኖ ሳይሆን ከጎን ሕፃን ሆኖ ነው። ትኩረቱ ማርያም እናቱ መሆኗ ላይና “የማርያም ልጅ” መባሉ ላይ ነው። ይህ አንድ አስተምህሮ ቢሆንም ለሚያየው ከአብ ጋር አንድ ስለ መሆኑ “የእግዚአብሔር ልጅ” ስለ መሆኑ የተሟላ ትምህርት አይሰጥም [ዮሐ 14፡9፤ 10፤30]። ወደ ኢየሱስ በቀጥታ መድረስ ይቻላል፤ ወደ አብ መቅረብ በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው [ዮሐንስ 14፡6]። የኢየሱስ መምጣት ምክንያቱና መሠረተ ትርጉሙ ይኸው ነው። ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ቅጥር በስተ ውጭ ተሰቀለ፤ በመስቀል ላይ ሆኖ “ተፈጸመ” አለ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃ “ከላይ እስከ ታች ተቀደደ” [ማቴዎስ 27፡51]። ሰው ወደ አምላኩ የሚቀርብበት የዘላለም መንገድ ተከፈተ። ማርያም ከዮሐንስና ከሌሎች ሴቶች ጋር ከመስቀሉ ግርጌ ቆማ “ተፈጸመ!” ብሎ ሲጮኽ ትሰማና ታይ ነበር። በልቧ ስታሰላስል የኖረች፤ “በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” የተባለች በዐይኗ ፊት ተፈጸመ [ሉቃስ 2፡35]። እውነትም “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” [ሉቃስ 1፡28፣42]፤ አሜን።

እሑድ በማለዳ ግን ሐዘን የሚያስረሳ ሰማይና ምድርን የሚያናውጥ የምሥራች ተሰማ፣ ታየ። ብዙዎች የዐይን ምስክሮች ነበሩ። ኢየሱስም በዐይን ምስክሮች ፊት ወደ አብ አረገ። ባረገ በአስረኛው ቀን የገባውን ተስፋ መንፈስ ቅዱስን ላከ። በኢየሩሳሌም በአንድነት በጸሎት ይተጉ የነበሩ ማርያምን ጨምሮ 120 ነበሩ [የሐዋርያት ሥራ 1፡21፤ 2፡1-]። መንፈስ ቅዱስም ወረደባቸው። ኢየሱስ የነገራቸውን ሁሉ የሚያስታውሳቸው መንፈስ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው መንፈስ፣ አጽናኝ የሆነ መንፈስ ወረደ። “የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፣ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፣ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና” የተባለለት መንፈስ ወረደ [ዮሐንስ 16፡12-15]። እውነቱን በእውነት የሚሹትን ወደ እውነተኛው የሕይወት መንገድ የሚመራ የእውነት መንፈስ ተሰጠ።

ሌሎች ጉዳዮችም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተዘዋዋሪና በቀጥታ ተካትተዋል። 1/ከኢየሱስ ሌላ አማላጅ እንደሌለ፤ 2/ማርያም ድንግል ሆና እንደ ኖረችና እንደማትመለክ፣ ወዘተ። ወንድማችን ዶ/ር ወዳጄነህ ቃል በገባልን መሠረት በስነ መለኮታዊ መረጃዎች የተደገፈ ሁለተኛውን እትም እንዳሳተመ የቀረውን ሐተታ እናቀርባለን። እግዚአብሔር ወንድማችንን በአገልግሎቱና በሕይወቱ ይባርክ፤ ለሕዝቡም ማስተዋልን ይስጥ።                         

ምትኩ አዲሱ