ጣልቃ እየገባ፣ ትንግርት ረገለት ሰው ትውስታ - በቀለ ወልደ ኪዳን - 2005 ዓ.ም. - 345 ገጽ። ሐተታና ግምገማ - በምትኩ አዲሱ

beqelebkcvr

መጽሐፍ መጻፍ የአንድ ሰው ብቻ ኃላፊነት ሊሆን አይችልም [ገጽ 5]። የጸሐፊ ተግባር ብቻ የሚያስቀር በመሆኑ የሚያስከፍለውን ዋጋ ሽሽት በጊዜ እጦት የሚያመኻኙ ጥቂቶች አይደሉም። ወንድም በቀለ ደክሞ ስላስነበበን መጽሐፍ እንኳን ደስ ያለህ ሊባልና ሊመሰገን ይገባል። ባስነበበን በዚህ መጽሐፍ ዙሪያ የኛስ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? በመጀመሪያ በጥረቱ ላይ ተጨምረን በዕንቡጥነት የተዋቸውን አሳቦች እንዲያብቡ ማገዝና፣ በተለይ መሪዎችና የመጻፍ እቅድ ያላቸው እንዲወያዩበት አደባባይ ማውጣት ነው። ይህንኑ በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ፣ በደራሲ ግዴታ ዙሪያ፣ ማሕበራዊ ኃይላት ከሚያሳድሩት ጫና አንጻርና ሊበረታቱ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ባጭሩ እንነጋገርባቸዋለን። ወንድም በቀለ መጽሐፍ ማንበብ ከሚወዱ ጽፈው ለማስነበብ ከሚጥሩ ጥቂቶች መካከል የሚደመር ነው። “ትውስታ” ብሎ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የ71 ዓመት [ሁለት መንግሥታት ፈጅቶ ሦስተኛውን የተያያዘ] የሕይወቱን ታሪክ ከሞላ ጎደል ተርኮልናል። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ሰባት ወዳጆቹ ለደራሲው ያላቸውን አስተያየት አድምቀው መስክረዋል። እኔም በተባለው ላይ እንዳልጨምር ግለሰቡን በግንባር ስለማላውቅ ትኩረቴ ባልተነካው በታሪኩ ይዘት ላይ ብቻ ይሆናል።

መጽሐፉን አንዴ በግርድፉ ሁለተኛ ጊዜ በዝግታና በጥልቀት አንብቤአለሁ። ከጅምሩ የታዘብኳቸውና ተስፋ የሚሰጡ የምላቸው እውነቶችን ላስቀድም። 1/ በደራሲውና ጳውሎስ በተሰኘ ወጣት መካከል ያለው ቅርርብ ሊበረታታ የተገባ ነገር ግን የተዘነጋ አገልግሎት ነው። ታናሹ “ለሽማግሌው ጓደኛዬ” ማለት መቻሉና ታላቁ በመጽሐፉ ዝግጅት ላይ እንዲያግዘው መጠየቁ ትሕትናና አክብሮትን አመልካች ነው [ገጽ 6]። ወጣቱ ትውልድ በጭፍንና በግብታዊነት ሲሮጥ የታጠቀው እንደሚፈታና ቅርሱ እንደሚባክን አያውቅ ይሆናል። በጳውሎስና ጢሞቴዎስ፣ በጳውሎስና በቲቶ፣ በበርናባስና በማርቆስ፣ በሙሴና በኢያሱ፣ ወዘተ የተመሰከረው የወንጌልን አደራ ለተተኪው ትውልድ ማቀበል አማራጭ እንደሌለው ነው። ዛሬ ትውልዱ ሰማንያ በመቶ ያህሉ 40 ዓመትና በታች [ወጣት] ነው። ወጣቱ በጌታ ጸጋ የቀደሙትን ለማድመጥ ፈቃደኛ ነው? የቀደሙትስ ሕይወታቸው ግልጽና ትሑት ነው? 2/ ደራሲው “ምሥጢር” የሆኑ የሕይወቱን ክፍሎች ለሌሎች ትምህርት እንዲሰጡ አስቦ መዘገቡ ትልቅ ጸጋ ነው። 3/ ጥሪ ሁኔታን አመቻችቶ ራስን መጥራት ሳይሆን ጠሪው ጌታ በወሰነው ሰዓት መሆኑን፣ ያንንም በቤተክርስቲያኑ በኩል እንደሚያደርገው ከራሱ ልምድ በመነሳት መስክሮልናል። 4/ ደራሲው ባለፈባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የጸጋን ብዛት አይተናል፤ አለዚያማ - በትዳር ውስጥ፣ ከትዳር ውጭ፣ በአገልግሎት - ከውስጥ እላቂ ጨርቅ ለብሶ ከላይ ሱፍ ደርቦ - የሕይወትና የአገልግሎት ምስክርነት ጠብቆ መቆም እንዴት ይቻላል? 5/ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን መጽሐፍ እንዲጽፍ ሙሉ ፈቃድ መስጠቷ። ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ባሕል ማጠናከር ቢችሉ፣ በግል ሆነ በጋራ በዓይነተኛ ጉዳዮች ላይ ሊጽፉ የሚችሉትን ለማሰባሰብ ይረዳል። ከዚህ ቀደም በዚሁ ድረገጽ እንዳስታወቅነው የንባብን ባሕል በቤተክርስቲያን ውስጥ ለማሠረጽ ዓመታዊ የመጽሐፍና የንባብ ቀን መመደብ አንዱ መንገድ ነው። ቤተመጻሕፍት ማደራጀትና የንባብ ክበቦችን ማቋቋም ሌላኛው ነው። በተለይ የማንበብ ብርቱ ፍላጎት እያላቸው የመግዢያ አቅም ላጡ ይህ አስቸኳይ መፍትሔ ይሰጣል። መጽሐፍ ሲባል “መንፈሳዊ” ብቻ ሊሆን አይገባም። ወንጌልን ለማዳረስ የዓለምን ድምጽ ማዳመጥ አማራጭ የለውምና። 6/ ወንድም በቀለ ገጣሚም ነው፤ ወደ ጌታ ሲመጣ ከእናቱ የወረሰውን የቅኔ ስጦታ ወደ ጎን አድርጎ፤ የጫጫራቸውን እስከ ማቃጠል ደረሰ [ገጽ 113፣ 285]።

ልቤን ከነኩት መካከል “ግጥሞቼን ካቃጠልኳቸው ይህችን መጽሐፍ በምጽፍ ጊዜ 35 ዓመታት አልፈውኛል” ያለው ነው [ገጽ 113]። ቤተክርስቲያን ስለ ኪነ-ጥበብ ያላትን ስነ-መለኮታዊ መረዳት እንዴት ትመርምርና ታዳብር? የስነ-ጽሑፍ መመዘኛው በሃይማኖታዊ ቃላት መታነጹ ነው ወይስ እውነትን ማንጸባረቁ? ዘማሪዎች ግጥም ብለው በሚዘባርቁበት ዘመን ሥርዓትና ለዛ ያለው ግጥም የሚገጥሙ አለመገኘት ልኩን ለማስተማር አዳግቷል። የሚቀጥለው መጽሐፉ የቀድሞዎቹንና አዳዲሶችን ያካተተ የግጥም መድበል እንደሚሆን ተስፋ እናደጋለን። 7/ በሠራተኛነት ተቀጥረው እቤቱ የገቡት ወደ ክርስቶስ ቤተሰብ መቀላቀላቸው ለወንጌል ኃይልና ውበት ምስክር ብቻ ሳይሆን ለቤት ሠራተኛ ያለውን ዝቅተኛ ግምት የሚያርም ነው። 8/ የፊደላት ግድፈት አለመኖራቸው ሌላው ተኣምር ነው። ስነ ጽሑፍን ከማሳደግ አንጻር ደግሞ ጠንካራ አርታኢና ሃያሲ መኖር አማራጭ የለውም። ከመሞጋገስ አልፎ ደራሲን ተጠያቂ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ሊኖር ይገባል። አንዱ መሪነትን ወይም ቤተክርስቲያንን በሚመለከት ቢጽፍ ሌላው ክተት አዋጅ የተባለ ይመስል መረባረብ ያስቸገረ ያሰለቸ አባካኝ ባሕል ሆኗል። የሚያስገርመው በተመሳሳይ ርዕስ ላይ የሚቀርቡ መጻሕፍት በሌላው ላይ የሚጨምሩት እምብዛም የላቸውም፤ ከአገሬው እውነታ ጋር አለማገናዘብ ሌላው ድክመት ነው። ይህ ግምገማ በትንሹም ቢሆን ይህን ጉድለት ያሟላ ይሆናል።

የቋንቋ አጠቃቀም ለአንባቢው አቅም መመጠንና መልእክትን በግልጽ ማስተላለፍን ይመለከታል። አንድ ደራሲ ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ቢያንስ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ መሻት ይኖርበታል። 1/ የምጽፈው ስለ ምንድነው? 2/ የምጽፈውን እንዴት ብገልጸው ይሻላል? በራሴ ድምጽ፤ በስድ ንባብ፣ በታሪክ መልክ ወይስ በልብ ወለድ መልክ ልጻፍ? ወዘተ። 3/ ምን ላካትት፣ ምን ላስቀር? 4/ አንባቢዬ ማነው? የመረዳት ችሎታውስ? ወዘተ። አንድ አሳብ የጸሐፊው ነው የሚባለውና ስለሚጽፈው መረዳቱ የሚረጋገጠው “ተራውን ሰው” ማነጋገር ከቻለ ነው። በዚህ ዘመን ግራ ያጋባ ነገር እንግሊዝኛ በአማርኛ ላይ በአደባባይ እያደረሰበት ያለው መንገላታት ነው። ይህን እንግልታማርኛ ብለነዋል። በአማርኛ አሳብን ማቅረብ ሲቻል፤ቃል በቃል እንኳ ባይሆን በሐረግ ሲቻል። የመጽሐፎችን ርዕስ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ማተም አዲስ ፈሊጥ ሆኗል፦ “የማርያም ታላቅ አእምሮ = The Great Mind of Mary። ልውጠታዊ መሪነት = Transformational Leadership። ሚዛን የጠበቀ ሕይወትና አገልግሎት = A Balanced Life and Ministry። የሚፈለግ መሪ = In Search of a Leader።” ወዘተ። እንግሊዝኛ መስሎት መጽሐፉን ሲገልጠው ውስጡ ጣል ጣል ከተደረጉ እንግሊዝኛ ቃላት በቀር አማርኛ ነው። አማርኛ ተናጋሪ ሲገልጠው ላዩ እንጂ ውስጡ ሌላ ሆኖ፤ የእንግሊዝኛ አባባሎችን ተሰባጥረው ያገኛቸዋል። ይህም የዘመኑ መንፈስ ተምሳሌት ነው እንበል። እኛ ግን ወንጌልን ምስክር እንጠራለን፤ ወንጌል የተጻፈው ለጥቂቶችና ለሊቃውንት ብቻ አይደለም። ወንጌል የተጻፈው  ለሁሉም ነው። ኢየሱስ የተገለጠው ለእረኞች ነው፤ ትሑታን ለሆኑ ጠቢባንና ደቂቃን ነው። ረቂቁ በማያጠራጥር በማያሻማ አኳኋን በሥጋ የተገለጠው ለፍጥረቱ ሁሉ ነው፤ ለእውነት ለሚመሰክሩ ሁሉ ምሪት ይሆናቸው ዘንድ ይህ ሆነ።   

ጥቂት ያይደሉ የወንጌል አገልጋዮች ስነ መለኮታዊ ይዘታቸው በተመናመነ ጥራዝ ነጠቅ ቃላት ሰሚውን ሲያደነቁሩ ይደመጣል። ለ“ተራ ምዕመን” የማይመጥኑ አሳቦች በመደርደራቸው ተናጋሪና አዳማጭ ሳይግባቡ ይኖራሉ። አድማጭ የሰማውን መልሶ እንዲናገር ዕድል ቢሰጠው ምን ያህሉ ከተነገረው ጋር ይቀራረባል? ወንድም በቀለ የመጋቢነት ጥሪ በቀረበለት ሰዓት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያሳለፈውን 10 የጭንቅ ቀናት ከ1909ኙ የፔትሮግራድ ሽብር ጋር ማያያዙን። ወይም “ከፈረሱ አፍ መስማት” ወይም “የደፏቸው ሁለት ባርኔጣዎች” የሚሉ አባባሎችን የሚ-ረ-ዱ ቢኖሩ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው [ገጽ 27፤ 102]። “ኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ፣” “ኢንቬስትመንት፣” “ሌጋሲ፣” “ትራንስፎርሜሽን፣” “ቪዥን፣” “ፊስካል ፖሊሲ” “ኖርማላይዜሽን” ወዘተ ከአገር መሪዎችና ከጋዜጠኞች ተደጋግሞ የሚሰሙ ቃላት ናቸው። አድማጩም ትርጉሙን ቢረዳ ባይረዳ እንደ ጸሎት ይደጋግመዋል። “ክራይቲርያ”ን “ክናቴራ” እንዳሰኘው አብዮተኛ። ይህ መጤ ባሕል ቤተክርስቲያንም ውስጥ ዘልቋል።

መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛና በጀርመን ቋንቋዎች መተርጎሙ ለቋንቋው፣ ለማሕበረሰቡ ባሕልና ሕልውና መገንባት፣ ለሳይንስ ጥበብና ለኢኮኖሚ መደርጀት ዋነኛ አስተዋጽዖ እንዳደረገ የታወቀ ነው። የሼክስፒርና የገርተን፣ የጋሌሌዮና የአይዛክ ኒውተንን ሥራዎች ከዚህ ታሪካዊ ሂደት ውጭ ማሰብ አዳጋች ይሆናል። ለዚህ አባባላችን ካስፈለገ በ1912 የሞተውን ማክስ ቬይበርን እና በሕይወት ያለውን ዩርገን ሃበርማስን ምስክር መጥራት ይቻላል። ሁለቱም አማንያን ያልሆኑ ስመ-ጥር የማሕበረሰብ ሳይንስ ሊቃውንት ናቸው። የማሕበረሰቡን አስተሳሰብና ባሕል ስታንጽ የኖረችዋ ቤተክርስቲያን ተገላቢጦሽ በዓለም ቋንቋ ተጥለቅልቃለች። ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ የተጻፉ ሰነዶችን መመርመር የቤተክርስቲያን ተጽዕኖ ምን ያህል እንደ ተዳከመ ያመለክታል። የየካቲት ስድሳ ስድስት አብዮተኞችና አሁን የሚገዛው መንግሥት አንድ የተረዱት ነገር ቢኖር በማሕበራዊ ለውጥ ውስጥ ቋንቋ ያለውን ድርሻ ማጤናቸው ነው። አብዮታዊ አስተሳሰቦችን ማሥሠረጽ ብቻ ሳይሆን የማርክሳዊ መዝገበ ቃላት የወጣቱ መማሪያና መገበያያ ተደርገው ነበር። ባሁኑ ወቅት የቋንቋ ፖሊሲ በእንጥልጥል መተውና የትምህርት ፖሊሲ መፈረካከስ ማሕበራዊ አለመያያዝን እያባባሱት ነው። ወጣቱ ልክና ስሕተቱን፤ ኃፍረትና ማንነቱን፣ የእግዚአብሔር ፍርሃትና የሰው አክብሮት ምን እንደ ሆነ ሳያውቅ እያደገ ነው። በራሱና በብሔሩ ላይ ከማተኮሩ ብዛት ለ“ጎረቤቱ” ያለበትን ማሕበራዊ ግዴታ ዘንግቶታል፤ ራሱን ማዳን በልጦበታል። ከፊቱ የሞራል መቀመቅ ተጋርጦበታል። የአገር መሪዎችን ንግግር ላጤነ ለሕዝቡ ሳይሆን አንዳቸው ሌላውን በዕውቀታቸው ብዛት ለማስደነቅ የሚፎካከሩ አስመስሎታል። ቤተክርስቲያን የተሰጣትን የወንጌል አደራ ለይታ ማወቅና በቋንቋዋ አለመቀያየጥና በመልእክቷ ጥራት ማሕበረሰብን ወደ ጽድቅ ከመመለስ ውጭ አማራጭ የላትም።  

የቤተክርስቲያን መሪዎች አብዛኛዎቹ መጽሐፍ አይጽፉም፣ ይጀምሩና ዳር አያደርሱም፤ የተጻፈውን አያነብቡም [የኑሮ ውድነት፣ የታክስና የቀረጥ ፖሊሲ አለመሻሻል፣ ሳንሡር፣ የተሟላ የአታሚ አገልግሎት አለመኖር ለመጻፍና ለማንበብ ደንቃራ እንደ ሆኑ ሳንዘነጋ። የአብያተክርስቲያናት በጀት ለመሆኑ ምዕመን እንዲያነብ በአእምሮ እንዲጎለብት ሚዛናዊነትን ጠብቆ ይዘጋጃል?]። መሪዎች በዋነኛ ጉዳዮች ላይ አይጽፉም፤ የሚመሩአቸውን ጉባኤዎች አንባቢ ለማድረግ ጥረት አያደርጉም። ከመስማት ይልቅ በሚታየው ላይ። ከመጽሐፍ ይልቅ ድምጻቸውን የሚሰሙበትና ፊታቸውን የሚያዩበትን ዲቪዲ መርጠዋል። ባለፉት ሃያ ዓመታት ጆሮአችን ተደፍኖ ዐይን ብቻ ሆነን ይሆን? ዋነኛ ጉዳዮች ስንል ደቀመዝሙርነት፣ ክርስቲያናዊ ስነ ምግባርና የቤተክርስቲያንን ማሕበራዊ ድርሻና ግዴታ ማለታችን ነው፤ የወንጌልን አስተምህሮ ከአገራችን ባሕልና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ አንጻር መተርጎም መቻል ማለታችን ነው። እነዚሁ መሪዎች ከ“መንፈሳዊ” መጻሕፍት ውጭ አያነብቡም። “መንፈሳዊ” በአብዛኛው የሰሜን አሜሪካ ባሕላዊ ክርስትና ውጤቶች ናቸው። የኦሮማይን “መንፈሳዊ” ይዘት አይገነዘቡም። “ፍቅር እስከ መቃብር” ከቲቢ ኤን ይልቅ የኢትዮጵያን ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ ይዘነጋሉ። እውነትን ከቤተክርስቲያን ክልል ውጭ ማሰብ ሆነ ማየት ይፈራሉ። ሊሰሙት ከሚሹት ውጭ ማስተናገድ አይፈቅዱም። በሰከነ አእምሮ ከመወያየት ይልቅ በአንጃ መካለልን ይመርጣሉ። ከቤተክርስቲያን ውጭ እንዳሉቱ ማለት ነው። ባጭሩ፣ መሠረተ ዓላማን በስፋት አለማየትና ከጋርዮሹ ይልቅ ለግል “ራእይ” [ምቾትና ምኞት] መሯሯጥ ከዚህ ቀደም ያልታየ ክፍተት ፈጥሯል። ይህም የወንጌል አገልጋዮችን ሥልጣን ነስቶአቸዋል።

ወንድም በቀለ የተነሳበትን ዓላማ እንደሚገባ ተወጥቶታል? እንደ እኔ አስተያየት ቢያንስ ሦስት መጻሕፍት የሚፈጁ ጉዳዮችን ባንድ ላይ ማጨቁና ከመጀመሪያ ጀምሮ ከመተረክ ይልቅ እየጣጣፈ ማቅረቡ ኃይሉን አባክኖበታል [በ1934 ዓ.ም በወላይታ ተወለድኩ፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በ… አጠናቀቅኩ፣ ሥራ ተቀጠርኩ፣ ትዳር መሠረትኩ፣ የክርስቶስ ተከታይ ሆንኩ፣ ወዘተ። የመርኪና መጃ፣ የጥሩወርቅ መስፍን፣ የአማኑኤል አብርሃምን ግለ-ታሪክ ይመልከቱ።] ለእረኛነት መመረጡን ያስታወቀን ምዕራፍ 1 ላይ ቢሆንም የተመለሰበት ምዕራፍ 8 ላይ ነው። እየጣጣፈ ያስነበበን ምናልባት አንባቢው እንዳይሰላችና ቀልቡን ለመሳብ አስቦ ይሆናል እንበል።

አሁን የሚገዛው መንግሥት የዘረጋጋው “ፌዴራላዊ/ክልላዊ” መርህ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በተለያየ መልኩ ተጽእኖ አድርጓል። መካነ ኢየሱስ ማእከላዊነትን የጠበቀ የአደረጃጀት ልምድ ቢኖራትም ፈተና የሆነባት ቋንቋ ነበር። ለሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ደግሞ ቋንቋ ሳይሆን አደረጃጀትና ኃላፊነትን ለማጋራት ያልተዘጋጀ አሠራር ነበር። ወንድም አሸናፊ ዘማት “ያለ አጥቢያው ፈቃድ እና በቤተክርስቲያን ዕውቅና ሰጭነት” [ገጽ 292] ቤተክርስቲያን ባይከፍት ኖሮ 11 ዓመት የፈጀውና ያፋጀው ችግር ምን ያህሉ ይወገድ ነበር? የቤተክርስቲያኒቱን አመራር በአንድ ወይም በጥቂቶች እጅ መተው ያስከተለውን ችግር “በመሪዎች ስብስብ” መተካቱ ጠቃሚነቱ ምን ያህል ነው? ግልጽነት የሌለበትን አሓዳዊ አመራር፣ በ “ስብስብ” አመራር መተካት ተጠሪነትን ማዛባት አይሆንም? ለዚህ ማስረጃ የሚሆነንን ከገጽ 55-56 ላይ እንመልከት። ወንድም በቀለ በፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ ተጠርቶ የትራንስፖርት አበል እንደ ተሰጠውና። “ሳያነጋግሩኝ?” ብሎ እንደ ጠየቀ፤ ኋላም የ “ስብስቡ” ዋና ጸሐፊ፣ “… የወሰንነው ካነጋገርንህ በኋላ እንዲሰጥህ ነበር … ይህንኑ [ለፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ] ነግረናታል … አልተግባባንም ማለት ነው … ሰሞኑን እናነጋግርሃለን” መባሉን ጠቅሷል።   

ለመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ቋንቋ ፈተናዋ እንደ ነበረ ጠቅሰናል። ለሙሉ ወንጌል ደግሞ ፈተናዋ ግልጽ ያልሆነ የሥልጣን አደረጃጀትና የኃላፊነት ክፍፍል አለመኖር ነው ብለናል። ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያንስ? ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን እስካሁን የቋንቋን ወጥመድ ተሻግራ ዘልቃለች። “ደቡባዊነት” ከንግዲህ አይቀናቀናትም አንልም። የቃሉን መካከለኛነት እስከ ጠበቀችና የሰማንያ አምስት ዓመት ታሪኳን እስካልረሳች ድረስ ግን በጌታ ቸርነት ሌላውንም በድል ትሻገረዋለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ተስፋ ሰጭ ሆኖ ያገኘሁት የሙሉ ወንጌልን ሸክም በመካፈልና መፍትሔ በመሻት ረገድ የአብያተክርስቲያናት መሪዎች ያሳዩት ርብርቦሽ ነው።  በሙሉ ወንጌል መሪዎች መካከል የተከሰተውና 11 ዓመት የፈጀው የሥልጣን ፍትጊያ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ነው። የቀረበልን መጽሐፍ ታሪካዊ በመሆኑ፣ ወንድም በቀለም ከመሪዎቹ አንዱ ሆኖ ሳለ ይህን ዋነኛ ነገር ለታሪክ ጸሐፊዎች ይ-ተው ማለቱ አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም [ገጽ 290]። ሌላኛው፣ ማእከላዊነትን የጠበቀ ልምድና ግልጽ የኃላፊነት ክፍፍል ባልነበረበት ዘመን፤ “የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ” [ገጽ 291] በሙሉ ወንጌል ችግር መከሰቱ። ደርግን የተካው መንግሥት “ፌዴራላዊ” አደረጃጀትና ጎሠኛ ክልሎችን መመሪያ ከማድረጉ ጋር ያለውን ግንኙነት አለመመርመር ትልቅ ስሕተት ነው። ከቤተክርስቲያን ወጥተው ለተደራጁ ከ300 ለሚበልጡ “ሚኒስትሪዎች” መባዛት ምን አስተዋጽዖ አድርጓል? መንግሥት በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እንዲዳኝ መደረጉ። የፍትሕ ሚኒስቴር ስለ ሃይማኖት ድርጅቶች አስተዳደር፣ አስተምህሮና ባለ ሥልጣናት አሿሿም ከነደፈው እቅድ አንጻር እንዴት ሊታይ ይገባል? [መንግሥት ሕገ መንግሥት ከሚፈቅድለት ውጭ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመራር ማደራጀቱ፣ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ይኸው መመሪያ ችግር ማስነሳቱ፤ “አክራሪ ሃይማኖተኛነትን” ለመቃወም ነሐሴ 21/2005 በአፍሪካ አዳራሽ የተካሄደው ስብሰባና ነሐሴ 27/2005 የጠራው አስቸኳይ ሰላማዊ ሰልፍ።

ፌዴራል ፍትሕ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት መሪዎችን አስጠርቶ የውስጥ መመሪያ ማርቀቁን ሲያስታውቃቸው ከአስተምህሮአቸው ጋር እንደማይስማማ መግለጻቸውና ጉዳዩ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ በወንጌላውያን መካከል፣ በወንጌላውያንና በመንግሥት መካከል፣ በወንጌላውያንና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል ሊከሰቱ ለሚችሉ ክፍፍሎች ምን ፍንጭ ይሰጣል? በደርግ ዘመን በ“ሃይማኖት አይለያየንም” ሳቢያ መንግሥት የተለያዩ ድርጅቶችን ከሚያራምደው አገራዊ “ሰላምና ልማት” መመሪያ ጋር ለማስማማት ያደረጋቸውን ሙከራዎች ባንረሳ። በተነደፈው አሠራር ላይ ጥያቄ ያስነሡትን አብያተክርስቲያናት የባእድ መንግሥት ጀሌዎች፣ የሰላምና የአገር እድገት ጠር ብሎ ፈርጇቸው እንደ ነበር ማስታወስ ከታሪክ መማር ነው።  

መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ሌላኛው አሳብ በስደት ምድር የተሰባሰበው ሕዝባችንና የወንጌል አገልግሎት ጥራት ጉዳይ ነው። መንጋ ሳይኖር እረኞች ለምን በዙ? ተጠሪነት የሌላቸው ራሳቸውን የጠሩ ወይም በባልንጀሮቻቸው የተጠሩ ተዘዋዋሪ/ተባራሪ አገልጋዮች በቃሉና በግል ሕይወታቸው ምን ያህል ታማኞች ናቸው? ኗሪነታቸው በውጭ የሆኑ የአገልግሎቶች መሪዎች አገር ውስጥ ካለችው ቤተክርስቲያን [የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት] ጋር እንዴትና ለምን ተባብረው ሊሠሩ አልቻሉም? የወንጌላውያን ማሕበራትስ መጠሪያና አድራሻ በትክክል ተመዝግቦ አለ ወይ? እየተዘዋወሩ የሚያገለግሉስ የት የት ምን እንዳስተማሩ መመዝገብና መዘገብ ቢቻል ተጠያቂነትን ማጠንከር ብቻ ሳይሆን የአስተምህሮን ጥራት መጠበቅ አያስችልም ወይ? እየተሽለኮለኩ የሚበዘብዙትንና መንጋን የሚያመሳቅሉትን ላለማስተናገድ መፍትሔው ምንድነው? ወዘተ።

“ጣልቃ እየገባ” የቀሰቀሳቸው ሌሎች ጉዳዮች ቢኖሩም ዴሞክራሲን በተመለከተ ያነሳውን ሳንመለከት አናሳርግም። “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ ሥርዓት … ይመስለኛል … በባህላችን ውስጥ የሌለ ነገር! ያላደግንበት፣ ያልኖርንበት፣ ያልተቃኘንበት ነገር! … እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለን ድርቅ የምንለው ነገር፤ አሳቦቹን ጥለን ባለ አሳቦቹን ጥምድ የምናደርገው ነገር” ብሎታል [ገጽ 223]። ምርጫ 97 እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ይዘት የታየበት ነበር። የሕዝቡ ጨዋነትና ተሳትፎ፣ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከየጎራው የሠለጠነ ክርክር የተደመጠበት ወቅት ነበር። መንግሥት ለዓለም ሕዝብ ዴሞክራሲን በማስፋፋት ረገድ ያደረገውን ተሞክሮ በኩራት ያስመሰከረበት ሁኔታ ነበር። በምርጫው ሰሞን በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ጋዜጦች የተዘገበውን ወደ ኋላ ሄዶ መመልከት በቂ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ገና ይቀረዋል፤ ዴሞክራሲ ባሕላችን አይደለም ማለት የተጀመረው ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ነው። ዴሞክራሲ ግን የተሠዋወረ ነገር አይደለም፤ የሰው ሁሉ መሠረታዊ ጥያቄ ነውና። ለዚህም ነው የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ረገጣ በአገር ሉዓላዊነት ሊሳበብ አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው። አንድ ሕብረተሰብ ንጽሑን ኮንኖ ወንጀለኛውን ነጻ ቢለቅ፤ ወይም ሁለት ወንጀለኞችን አንዱን ነጻ ለቆ ሌላኛውን ቢቀጣ። የሥራ የሥልጠናና ቤት ንብረት የማፍራት እድል ለአንዱ ፈቅዶ ለሌላው ቢነፍገው፤ ለምን ይህ ሆነ የማይል ሕዝብ የለም። መንግሥትና ሕዝብ የሚተዳደሩበት ውል አላቸው፤ ሕገ-መንግሥት በመሠረቱ ለመንግሥትና ለሕዝብ መብትና ግዴታን የሚደነግግ የውል ሰነድ ነው፤ ይህን ውል የሚያፈርሰውን መሪ ይሁን ተመሪ ሳያዳላ ይቀጣል። አንድ ሕዝብ አሳቡን ሳይፈራ የመግለጽና ፈጣሪውን ሥርዓቱ በሚደነግግለት መሠረት የማምለክ፣ በማሕበር የመደራጀት፣ መሪዎቹን የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው። ዕድር፣ ዕቁብ፣ ጂጊ፣ አፈርሳታ ከመገለጫዎቹ መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ገና ይቀረዋል ማለት የተጋነነ ብቻ ሳይሆን መሠረት የሌለው የፖለቲከኞች ጫወታ ነው። ለመሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ ባሕል የሚዳብረው እንዴት ነው?

የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ለእውነት እንድንመሰክር ተጠርተናል። ኢየሱስን አስቀድመን፣ በመስቀሉ ትይዩ ቆመን፣ መስቀሉን ተሸክመን ለግራ ለቀኝ በማይል በጽድቅ መንገድ ላይ የምንጓዝ ነን። የተቀበልነው ወንጌልና መንፈስ የእውነት መንፈስ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ፍርሃት የማያውቅ መንፈስ አለን። ሰው ክቡር ነው፤ ሰው ክቡር የሆነው በአምላኩ አምሳል ስለ ተፈጠረ ነው፤ ሰውን አለማክበር እግዚአብሔርን አለማክበር የሚሆነው ከዚሁ የተነሳ ነው። ዴሞክራሲ ሰውን ያማከለ እንደ መሆኑ ክርስቲያናዊ ነው ባይባልም ለሰብዓዊነት በነፍስ ወከፍ ያለው አክብሮት ከክርስትና ብዙም የራቀ አይደለም እንድንል ያስገድደናል። በከረመባቸው አገራት እንኳ ለየአዲሱ ትውልድ ዴሞክራሲ ምን ጊዜም እንግዳ መሆኑን አንርሳ። ዴሞክራሲ የማያቋርጥ ትጋትና እንክብካቤ ይፈልጋል። በአጼ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ላይ የተነሳው ተቃውሞ አንዱም ዴሞክራሲን ፍለጋ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የዴሞክራሲ ፍንጭ ታየ። ብዙም ሳይቆይ ጥቂቶች “ገና ይቀረናል፣ ባሕላችን አይፈቅድም” ብለው አማራጮችን ሁሉ ዘጋጉት። በፈንታው “መንግሥት ያውቅልሃል” አሉ። መንግሥትም እኔ ካልሁት ውጭ ወዮልህ! ትጠይቀኝና ወዮልህ! አለ። ደርግ ከወደቀ በኋላ እንደ ገና የዴሞክራሲ ደወል ተሰማ። አጀማመሩ ባያምርም 97 ላይ ትልቅ ተስፋ የሰጠ ታይቶ የማያውቅ አካሄድ ታየ። አርባ ዓመት [ሁለት ትውልድ ማለት ነው] የዴሞክራሲን ባሕል ለመገንባት ቢሞከር ኖሮ በደርግ ዘመን ለነበሩት እንኳ ባይደርስ ለዚህኛው ትውልድ ይተርፍ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ዴሞክራሲ በመጠባበቅ አይመሠረትም። አንድ ቦታ ላይ ሊጀመር ሲገባ፣ ሳይጀመር ጊዜው አልደረሰም ማለት ራስን መሸንገል ነው። ዴሞክራሲ የሠፈነባቸው አገራት አሉበት ለመድረስ የቻሉት፤ ባለ ሥልጣናት ካደረሱባቸው ግፍ ለመላቀቅና ከፍርሃትና ከእጦት ነጻ ለመውጣት ስለ ተነሡ ነው።  የቤተክርስቲያን ድርሻ በአንጃ ፖለቲካ መጠመድ ሳይሆን ነጻ የሚያወጣውን የወንጌልን ብርሃን በጨለማ ላሉ ሁሉ ማብራት ነው [በክርስቶስ ውስጥ የሌሉ ሁሉ በጨለማ ናቸው። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሏልና።] እውነትን ማስተማር፣ የጽድቅና የፍትሕን መንገድ ማሳየት ነው። ማሕበረሰብ በአደንዛዥ ዕጽ በሰዶማዊነት በሙስና በራስ ወዳድነት ተዘፍቆ ሲማቅቅ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን መልእክቷን እንዴት ማጥራት ይኖርባታል?

እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ማለት የሌለበት ማሕበረሰብ የለም። አሳቡን ትቶ አሳቡን ያመነጨውን መጣላትና ስም ማጥፋት ሁሉም ቤት አለ። ሰው ሲባል ራስ ወዳድ እንደ መሆኑ እነዚህ ባሕርያት ይከተሉታል። ዓይነተኛ የሆኑ ልዩነቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፦ በየትምህርት ቤቶች የሚገበየው እውቀት ምን ያህሉ አብሮነትን፣ እኩልነትን፣ ብቃትን፣ ፍትሃዊነትን። ባጭሩ፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን አካትቷል? [ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በዘጠኙ ክልሎች በ4ኛ፣ 7ኛ፣ 11ኛ ክፍሎች ቢያንስ የታሪክ/ሲቪክስ መማሪያ መጻሕፍትን መመርመር ይጠይቃል።] የሕግ የበላይነት ለሁሉም እኩል ይሠራል? የጊዜውን ፖለቲካ ከማራመድ ይልቅ በእውነት ላይ የተመረኮዘ ሚዛናዊነት ተጠብቋል? ቤተክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንጂ ከዓለም አይደለችም ማለት እንዴት ይተረጎማል? የቤተክርስቲያን ዋነኛና አሳሳቢ ጉዳዮች ምንድናቸው? ነገ የማይቻሉ ዛሬ ዝግጅት የሚሹ ጉዳዮችስ ምንድናቸው? እነዚህና የመሳሰሉት ጉዳዮች ብዙ ውይይት ያሻቸዋል።

ወንድም በቀለ ወልደ ኪዳን ከአያቶቹ ጀምሮ እግዚአብሔር ጣልቃ እየገባ በሕይወቱ ያደረገውን ነግሮናል፤ እኛም ከአዳም ጀምሮ በክርስቶስ በኩል ያደረገውን በቃልና በኑሮ እንድንናገር ጌታ ይርዳን።

ፍቅሩን አይቼ ቀምሸዋለሁ / ፍጹም ላመልከው ቃል ገብቻለሁ

በመከራዬ [ጣልቃ] እየገባ / ይጋፈጠዋል እንዳልረታ

አመልካለሁ ይህንን ታላቅ ጌታ / አመልካለሁ በማንም የማይረታ

አመልካለሁ ግንበኞች የናቁትን / አመልካለሁ የማዕዘን እራስን።