ዜና ዕረፍት
ወንድማችን አቶ ላቀው ተሰማ ሐምሌ 1923 ዓ.ም. በገሊላ ከተማ፣ ጋሞጎፋ ጠቅላይ ግዛት ከአባታቸው ከአቶ ተሰማ ጽድቄና ከእናታቸው ከወይዘሮ እህተሥላሴ አርጋው ተወለዱ። አባታቸው በኡጋዴን ጦርነት ስለሞቱባቸው በልጅነታቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ትምህርታቸውን መጀመሪያ በቤተክህነት፣ ቀጥሎ በመድኃኒዓለም እና በበየነ መርዕድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ። በተጨማሪ፣ በማታ ትምህርት የንግድ ሙያ ትምህርት ተከታትለዋል። ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ በ ኤስ አይ ኤም የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ላቀው በአስራ ስምንት ዓመት ዕድሜአቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ዳኑ። ከዚያም ሌሎችን ወደ ክርስቶስ እምነት ማምጣት ተቀዳሚ ተልእኮአቸው ሆነ። ኋላ፣ አዲስ አበባ ጌጃ ሠፈር “ቃለ ሕይወት” ቤተክርስቲያንን ከጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነው ለመመሥረት በቅተዋል። መጀመሪያ “መሠረተ ሕይወት” ኋላም “ቃለ ሕይወት” ብለው የሰየሙትም እርሳቸው ናቸው። ስደት ተነስቶ ሚሲዮናውያን ከአገር እንደ ወጡ፣ እቤታቸው አጠገብ የምትገኘዋን ጎፋ ወንድማማች ቤተክርስቲያን እንዳትበተን አማንያንን ስላሰባሰቡ ከቀበሌ ባለሥልጣናት መንገላታትና እሥራት ደርሶባቸዋል።
ባለቤታቸውን ወይዘሮ መንበረ ገብረ አምላክን በ1947 ዓ.ም. አግብተው አንድ ሴትና አራት ወንዶች ልጆች አፍርተዋል። በተጨማሪ ስምንት የአማንያንን ልጆች አሳድገው አስተምረዋል። አቶ ላቀው እሑድ ሌሊት ላይ አርፈው፣ ቀብራቸው ዛሬ ተፈጽሟል።
“የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።” [መዝሙር 116፡15]። እግዚአብሔር ቤተሰቡን ያጽናና። አሜን።

