ዓላማ መር ሕይወት
የክርስቶስን ወንጌል አገልግለው ወደ ጌታ ለሄዱት ለወንድማችን ለአቶ መስፍን ተስፋዬ መታሰቢያ ይሁን
ስለ መጽሐፍት ግምገማና ትርጉም በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ “የወንጌል ስርጭትና እስካሁን የተጓዝነው ጉዞ” በሚል ርዕስ በመጠኑ እንዲህ ብለን ጠቃቅሰን ነበር፦
“ምንም እንኳ የትችት ባሕል በቤተ ክህነት ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ በተለይ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ክልል የጽሑፎች ግምገማና ትችት ልምድ ይጐድላል። ትችት ሲባል ነቀፌታ እንጂ ክርስቲያናዊ ምግባር እንደሆነ አይታሰብም። ይህ ስህተት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የስነ-ጽሑፍ ትችት ለደራሲ እድገት፣ ለአንባቢ ጥቅምና ለስነ-ጽሑፍ ልማት አማራጭ የሌለውና ሊዳብር የሚገባ አገልግሎት ነው … በመሠረቱ፣ የአንድ ጽሑፍ ግምገማ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርበታል። የጽሑፉ መነሻ አላማና ዋነኛ መልእክት ባጭሩ ምንድነው? የደራሲውስ ብቃት? ጸሐፊው የተነሳበትን አላማ በሚገባ አስረድቷል? ዓይነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችንና ምሳሌዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል? በዚህ ጉዳይ ላይ የማናውቀውን አዲስ መረጃ አቅርቦልናል? ሊታከል ወይም ሊታረም የሚያስፈልግ ነገር አለ? የተራ አንባቢውን የመረዳትና የባሕል አቅም እንደሚገባ ተገንዝቧል? ባጠቃላይ የጽሑፉ ጠንካራና ደካማ ጐን የቱ ላይ ነው?” [በፈረንጅ አቆጣጠር ኦክቶበር 2006]
የ “ዳቪንቺ ኮድ” የተሰኘው መጽሐፍ በክርስቶስና በወንጌሉ ላይ የነዛውን መሠረተ-ቢስ ሃሳብ በማብራራትም ጽፈን ነበር። ዛሬ ደግሞ በእንግሊዝኛ ተጽፎ ወደ አማርኛ በተተረጎመ “ዓላማ መር ሕይወት” ላይ የመጀመሪያውን ግምገማችንን እንጀምራለን።
ግምገማና ገምጋሚ፦ ግምገማ ስንል በተሠነዘረው አሳብ ላይ ማወያየትን፣ የተዘነጋ ወይም የተዛባ ትምህርት ካለ ማከልን፣ ያልተጠቀሱ ነገር ግን የተቀራረቡ አሳቦችን ማሰባሰብን ይጨምራል። ዞሮ ዞሮ ዓላማው ማነጽ ነው:: የአንድ መጽሐፍ ደራሲ ለሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ጥንቃቄ እንዲወስድ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን ደራሲው ራሱ ከተጠያቂነት በላይ እንዳልሆነ ማስረዳትን ይጨምራል። ገምጋሚውም በተራው እንደ ግምገማው ጥራት መልሶ ስለሚገመገም ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። መጠባበቅና መደጋገፍ አንደኛው ጥሪአችን ነው። ባጭሩ፣ ማኅበረ ምዕመንን የሚመለከት ጉዳይ በአንድ ሰው ወይም በጥቂቶች እጅ መተው የለበትም ለማለት ነው። የዛሬው ግምገማችን ተራዝሞ ሌላ መጽሐፍ እንዳይወጣው በማሰብ በ “ዓላማ መር ሕይወት” ትርጉም ጥራት ላይ ብዙ አናተኩርም።
የመጽሐፉ ርዕስ፦ ዓላማ መር ሕይወት (በእንግሊዝኛ፦ The Purpose Driven Life)
ደራሲ፦ ሪክ ዋረን። ተርጓሚ፦ ኤቫንጄሊካል ቴዎሎጂካል ኮሌጅ፤ አዲስ አበባ
የታተመበት ዘመን፦ 1994 (በኢትዮጵያ)፤ 2002 (በፈረንጅ)።
የተተረጎመበት ዘመን፦ 1997 (በኢትዮጵያ)፣ 2005 (በፈረንጅ)
በአማርኛ ሦስተኛ እትም። የገጽ ብዛት 340። ገምጋሚ፦ ምትኩ አዲሱ
“ዓላማ መር ሕይወት” ‘ሳድልባክ’ በተሰኘ በካሊፎርንያ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ቤተክርስቲያን መጋቢ ሪክ ዋረን የተጻፈ መጽሐፍ ነው። እኝሁ ሰው ቀደም ሲል “በዓላማ የሚመራ ቤተክርስቲያን” የሚል ጽፈው ያስነበቡ ሲሆን ሁለቱም ከሃያ አምስት ሚሊዮን ኮፒ በላይ ተባዝተው ተሽጠዋል፤ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል። “በዓላማ የሚመራ ማኅበረሰብ” ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል በቅርቡ ይታተማል ተብሎአል። “ዓላማ መር ሕይወት” የሚከተሉትን መሠረታዊ አሳቦች ያዘለ ነው፦
በምድር ላይ የተገኘህበትን ምክንያት በራስህ ጥረት መረዳት አትችልም
ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ማወቅ ይኖርብሃል
እግዚአብሔር በዓላማ ለዓላማ ፈጥሮሃል
ዓላማ የሌለው ሕይወት ከሞት ይብሳል (ገጽ 32)
በዚህ መጽሐፍ የተካተቱትን 40 አጫጭር ምዕራፎች አንዳንድ በየቀኑ እያሰላሰልህ
ብታነብባቸው ዓላማ ያለው ደስተኛ ሕይወት ይኖረሃል፣ የሚል ነው።
ብዙ ሰዎች በግልና በቡድን ይህን የአርባ ቀን ጥናት ተከታትለዋል። በሩዋንዳ ደግሞ የሃይማኖትና የአገር መሪዎች ሳይቀሩ ተሳትፈውበታል። ውጤቱም እያደር መከሰቱ አይቀርም።
የትርጉም ሥራ ክብደትና ኃላፊነት፦ የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው። በመጀመሪያ፣ ተርጓሚው ቢያንስ ሁለቱን ቋንቋዎች (ለዚህኛው እንግሊዝኛና አማርኛን) አጥርቶ ማወቅ ይኖርበታል። የሁለቱን ቋንቋዎች ዘይቤ፣ ያልተገለጡ ነገር ግን የታሰቡ አሳቦችን፣ የሚተረጎምለትን ትውልድ ቋንቋና አስተሳሰብ፣ የደራሲውን ባሕል፣ ማንነትና መነሻ አሳብ፣ የአንባቢውን ዓይነትና የመረዳት አቅም፣ ዘመን የለወጠውንና ያጸናውን ባሕል፣ ወዘተ፣ ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪ፣ በአእምሮው ውስጥ አንዱ ቋንቋ ሌላኛውን እንዳይበርዝ፣ እንዳይቆጣጠር መጠንቀቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ ትርጉሙ የደራሲውን አሳብ በታማኝነት ሳያቀርብ ይቀራል፤ ሲብስም ለአንባቢው የፈረንጅ አማርኛ ይሆንበታል።
በመጨረሻም፣ ተርጓሚው አሜሪካዊ ክርስትና በአብዛኛው ባሕላዊ ክርስትና እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። ባሕላዊ ስንል ዲሞክራሲያዊ ባሕልና አስተሳሰብ የሠረጸበት ማለታችን ነው፤ የገበያ ኃይላት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ማለታችን ነው። ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ደግሞ ሁሉም እኩል እንደ ሆነ አድርጎ ማየትን የሚያገንን ነው። ይህ በአንድ ፊቱ መልካም ቢመስልም “እውነት እንደ አመለካከት ነው” ስለሚል በጥርጣሬ ሊታይ ይገባል። “ይኸ ስሕተት ነው፣ ይኸ ትክክል ነው” ብሎ ማለት የሰውን መብት መጋፋት ነው ስለሚል ልኩንና ስሕተቱን መለየት ያዳግተዋል፤ መድፈር ያቅተዋል። ፈተናው ብዙ ነው ያልነው ለዚህ ነው። ሌላ ሊዘነጋ የማይገባ ነገር ባሕላችን ከምዕራቡ ባሕል ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ለተጻፈበት ቋንቋና ባሕል የቀረበ መሆኑን ነው። ታዲያ ከሌሎች አንማርም አንልም። መማር ደግሞ የሌሎችን ልምድና አስተሳሰብ መዝኖ ከራስ ሁኔታ ጋር ማዛመድን ይጠይቃል። የትርጉም ሥራ ፈተናው ብዙ ነው፤ ጥቅሙም እንደዚሁ። የትርጉምን ሥራ ጥቅም መገንዘብ የምንችለው በተለይ ተተርጉሞ በእጃችን ያለውን ዘላለማዊውን

